በ2015 በጀት ዓመት ሊከናወኑ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት
በ2015 በጀት ዓመት ሊከናወኑ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውኑን የተቋሙ የበላይ አመራሮች በተገኙበት ከስራ ሂደት ኃላፊዎች እና ከሪጅን ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በመሆን በጥልቀት በመገምገም ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቹን መለየት ችሏል፡፡ ከዚህም በመነሳት አመርቂ ውጤት የተመዘገበባቸውን ስራዎች በ2015 በጀት ዓመት አጠናክሮ ለመቀጠልና ክፍተት የታየባቸውን ደግሞ በበለጠ ትጋት በማከናወን ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ በግምገማው ወቅት አፅንኦት የተሰጠው ጉዳይ ሲሆን፣ ተቋሙ በ2015 ለማከናወን ያቀዳቸውና ትኩረት የሚሰጣቸውን ተግባሮች በተመለከተ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደስራ ገብቷል፡፡
በአስተዳደሩ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ውስጥ በመደበኛነት እና በተጓዳኝ የሚሰሩ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ተቋሙ የተለየ ትኩረት በመስጠት ለማከናወን በዕቅዱ ካካተታቸው አንኳር ተግባሮች መካከልም የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ለማሻሻልና ተደራሽነቱን ለማስፋት በመረጃ ቴክኖሎጂ ግንባታ ላይ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ መስራት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ብሔራዊ የመለያ ቁጥር ስርዓት የጡረታ ባለመብቶች እንዲካተቱ ከኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ተቋም ጋር በጋራ መስራት፣ የጡረታ ባለመብቶች የሚያቀርቧቸውን የአገልግሎት መሻሻል ጥያቄዎች ላይ ጥናት በማካሄድ ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የጡረታ መዋጮ ገቢን ከ2014 በጀት ዓመት አንጻር በ21 በመቶ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ገቢን በ30 በመቶ ማሳደግ፣ የአስተዳደሩን ማቋቋሚያ ደንብ በማፀደቅ የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት ወደ መሬት ለማውረድ መስራት፣ ከአስተዳደሩ ማቋቋሚያ ድንብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የማስፈጸሚያ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለሚመለከተው የመንግስት አካል እንዲፀድቁ ማቅረብ እና ከሠራተኞች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ትኩረት የሚሰጣቸውና በአመራሩ የቅርብ ክትትል የሚደረግባቸው ናቸው፡፡
በ2014 በጀት ዓመት አስተዳደሩ ላስመዘገባቸው አበረታች ውጤቶች የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ያበረከቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ ሲሆን፣ በ2015 በጀት ዓመትም ሊከናወኑ በዕቅድ የተያዙ ተግባሮች በአመርቂ ውጤት የታጀቡ እንዲሆኑ በተሻለና ከፍ ባለ ትጋት ኃላፊነትን መወጣት ይጠበቃል፡፡ ተቋሙ አገልግሎት አሠጣጡን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ በኩል ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እንደተለመደው ሁሉ ለተቋሙ ስኬት ትብብራቸውን እንዲቀጥሉ እንጠይቃለን፡፡