አዲሱ የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ማውጣት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድናቸው?
አዲሱ የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ማውጣት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድናቸው?
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ፈንድ አስተዳደር የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሂዲን ጀማል እንደገለጹልን፣ ተቋሙ የሚሰበስበውን የጡረታ ፈንድ ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት በተመረጡና አዋጭ በሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራት እንደሚችል ተደንግጎ ነበር። ነገር ግን ተቋሙ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ብዙ ጊዜ ሲሳተፍ አይስተዋልም። በአዋጅ የተሰጠውን መብትም ወደ ሥራ ሳይቀይር ቆይቷል።
ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ተቋሙ ፈንዱን በአዋጭ ኢንቨስትመንት ላይ ለማዋል የግድ በሌላ ተቋም ይሁንታ ወይም በገንዘብ ሚኒስቴር ፈቃደኝነት ላይ የተንጠለጠለ ስለነበር ነው። በመሆኑም አዋጆቹን ማሻሻል ያስፈለገበት የመጀመሪያው ምክንያት አስተዳደሩ የሌላ ተቋም ይሁንታና ፈቃድ ሳያስፈልገው ወይም ሳያሻው እራሱን ችሎ አዋጭ የሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በመንግስት ፖሊሲ የተደገፈ ጥናት አድርጎ፤ ፈንዱን በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ማዋል እንዲችል ነው። ስለዚህ አዲሱ አዋጅ የመንግስት ሠራተኞች የጡረታ ፈንድን ቀጣይነትና አስተማማኝነት ከማረጋገጥ ባለፈ ፈንዱ በኢንቨስትመንት እንዲዳብርና ግልጽ የሆነ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖረው ያስችላል።
በመሆኑም ከጡረታ አበል ክፍያ የሚተርፈውን የጡረታ ፈንድ ገንዘብ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ በማዋል የጡረታ ፈንዱን ገቢ ማሳደግ እንዲቻል አስተዳደሩ ጥናት በማካሄድ አማራጮችን ማቅረብ ይኖርበታል። ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ የኢንቨስትመንት መመሪያ በገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚወጣ ተደንግጎ የነበረ ቢሆንም፤ በሚኒስቴሩ መመሪያ ባለመውጣቱ፣ በመርህ ደረጃም የጡረታ ፈንድ የአደራ ገንዘብ በመሆኑ እራሱን በቻለና በመንግስት በሚመደብ የሥራ አመራር ቦርድ መመራት ስለሚኖርበት በአዲሱ አዋጅ ንዑስ አንቀጹ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡
የሥራ አመራር ቦርዱ በተቋሙ ተጠንቶ የቀረበለትን አማራጭ የመንግስትን የፋይንስና የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ሕጎችን በመከተል መወሰን እንደሚኖርበት በድንጋጌው ተጨምሮ ገብቷል፡፡ በአስተዳደሩ በሚወሰኑ አትራፊና አስተማማኝ ኢንቨስትመንቶች ላይ ፈንዱን በማዋል ዘላቂነቱንና አስተማማኝነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባም በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል።
ሁለተኛው አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት የተቋሙን አደረጃጀት እና ቁመና ለመቀየር የሚያስችል የሪፎርም ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በተጠናው ጥናት ተቋሙ የሚሰበስባቸውና የሚያስተዳድራቸው ፈንዶች ቢኖሩም በመሠረታዊነት ሲሠራ የነበረው አስተዳደራዊ ስሥራዎችን ነበር። ነገር ግን የተቋሙ ባሕሪ ከአስተዳደራዊ ሥራዎች ባሻገር የፋይናንስ ሥራዎችን ጭምር ይሠራል። ስለዚህ ተቋሙ የአስተዳደር ዘርፍ ላይ ብቻ የሚሳተፍ ተቋም መሆን የለበትም። አንድ ደረጃ ወደፊት መምጣት አለበት የሚል ምክረ ሀሳብ በጥናቱ ግኝት ቀርቧል። በጥናቱ መሰረት በአዲሱ አዋጅ ተቋሙ ወደ ከፊል ፋይናንስነት ሊያድግ ችሏል፡፡ ከዚህ በፊት ተጠሪነቱ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የነበረውን በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ መሆኑንም የህግ ባለሙያው ተናግረዋል።
በዋናነት አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱ ምክንያቶች እንደሆነ አቶ ሙሂዲን ጠቅሰው፤ ቀድሞ የነበረው አዋጅ ሥራ ላይ በሚውልበት ወቅት የሚነሱ አንዳንድ የፍትሃዊነት ጥያቄዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲባል በአዲሱ የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ላይ ተሻሽለው የወጡ ድንጋጌዎች አሉ። ከዚህ ውስጥ በትርጓሜ ላይ የተደረገ ማሻሻያ አንዱ ነው።
በትርጉም ላይ ከተደረጉ ማሻሻያዎች ውስጥ ‹‹ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ሥራ›› ማለት በመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ በመንግሥት የልማት ድርጅት ወይም በመንግሥት በሚካሄድ ፕሮጀክት ወይም ፕሮግራም ውስጥ በጊዜያዊነት ወይም ለቁርጥ ሥራ ከ60 ቀናት ላላነሰ ጊዜ በመቀጠር በየወሩ ደሞወዝ እየተከፈለበት የሚከናወን ሥራ ሲሆን፤ በቀን ሥራ፣ በጥጥ ለቀማ፣በሸንኮራ አገዳ ቆረጣ እና ሌሎች መሰል በየዓመቱ እየተደጋገሙ የሚከናወኑ ሥራዎችን አይጨምርም በሚል ተደንግጓል።
ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ ከ45 ቀናት ላላነሰ ጊዜ የሚለው። በአዲሱ አዋጅ ወደ 60 ቀናት ከፍ ተደርጓል። ስለዚህ ከላይ ከተጠቀሱት በየዓመቱ እየተደጋገሙ ከሚከናወኑ ሥራዎች ውጭ አንድ ሰው በሌሎች ሥራዎች ለ60 ቀናት ተቀጥሮ የሚሠራ ከሆነ የጡረታ መዋጮ ይቆረጥበታል። ይሄንን ሁሉም የመንግስት መሥሪያ ቤቶች አውቀው ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሌላው ከሠራተኞች መብት አኳያ አንዳንድ የመንግስት ሠራተኞች በራስ ፍቃድ በ25 ዓመት አገልግሎትና በ55 ዓመት ዕድሜ በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በዚያው በነበሩበት መስሪያ ቤት በመቀጠር ደሞወዝ እና የጡረታ አበል በመቀበል ያለአግባብ ተደራቢ ጥቅም የሚያገኙ አሉ፡፡ ይህ ከጡረታ መውጫ ዕድሜ አምስት ዓመት አስቀድሞ በራስ ፍቃድ መውጣት እንደሚቻል የተደነገገውን ያለአግባብ በመጠቀም የጡረታ አበልና ደመወዝ አጣምረው እየተቀበሉ በዛው በነበሩበት መስሪያ ቤት በፕሮጀክትና ፕሮግራም በመቀጠር በሌሎች ሥራ ፈላጊ ተወዳዳሪዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ተጽዕኖ እንዲፈጠርና የመልካም አስተዳደር ችግር እያስከተለ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል ተጨማሪ ንዑስ አንቀጽ እንዲገባ ተደርጓል፡፡
ይህም አዋጁ ከጸናበት ቀን አንስቶ ወደ ፊት ዕድሜው 60 ዓመት ከመሙላቱ በፊት በራስ ፍቃድ የአገልግሎት የጡረታ አበል መቀበል የጀመረ የመንግሥት ሠራተኛ በዚያው የመንግስት መሥሪያ ቤት (ድርጅት) ከተቀጠረ ይከፈል የነበረው የጡረታ አበል እንደሚቋረጥ በአዲሱ አዋጅ መደንገጉን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 15/2014