19ኛው ዓለም ዓቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ

19ኛው ዓለም ዓቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ተከበረ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አመራሮችና ሠራተኞች 19 ኛውን ዓለም ዓቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን ህዳር 23 ቀን 2015 "ሙስናን መታገል በተግባር!" በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት አከበሩ፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳባ ኦሪያ እንዳሉት የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እና ሙስናን ለመታገል የተለያዩ ተግባሮችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሠራተኞችን ግንዛቤ ለማሳደግም በስራ ላይ ስነ ምግባር እና በሞራል ዕሴት ግንባታ ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኞች የሀብት ምዝገባ፣ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት እና የአሠራር ስርዓት ጥናት የተከናወኑ ሲሆን፣ ሙስናን አስመልክቶ ጥቆማ ሲደርስም በማጣራት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በተቋሙ ውስጥ ከሥራና ከአሠራር ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ እንዲሁም ህጎች ሲጣሱ በስልክ፣ በአካል እና በሌሎችም መንገዶች ጥቆማ በመስጠት፣ ጥያቄ በማቅረብ እና አስተያት በመስጠትም ጭምር በመሳተፍ በሙስና መከላከል ንቅናቄው ላይ ድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

በዕለቱ በዓለም ለ19ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ "ሙስናን መታገል በተግባር!" በሚል መሪ ሃሳብ በተከበረው በዚህ በዓል ላይ በሙስና መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ፅሁፍ ለውይይት ቀርቧል፡፡ ሙስና ውስብስብ የሆነ፣ ታስቦበት እና ታቅዶበት የሚከናወን ወንጀል መሆኑን በመድረኩ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ሙስናን መጠየፍ፣ መከላከል እና መጠቆም ከሁሉም ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የፀረ- ሙስና ቀንን ዕለቱን ብቻ ጠብቆ ማክበር ብቻ ሳይሆን፣ ሙስናን ለመታገል የገባነውን ቃል በማደስ እና ተሳትፏችንንም በማሳደግ ጭምር አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን ያሉ ሲሆን፣ ሁላችንም በመንግስት የተሰጠንን ኃላፊነት በጥብቅ ዲሲፕሊን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ የበዓል ዝግጅት ላይ ግጥሞች የቀረቡ ሲሆን፣ በመድረኩም የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተካፍለዋል፡፡

 

Share this Post