አስተዳደሩ 50ኛውን ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን በድምቀት አከበረ

አስተዳደሩ 50ኛውን ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን በድምቀት አከበረ

=====//=========

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አመራሮች እና ሠራተኞች "50ኛ ዓመት የሴቶች ድምጽ ለዕኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በሀገራችን ለ50ኛ ጊዜ የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ በዓል መጋቢት 04 ቀን 2018 በዋናው መስሪያ ቤት በድምቀት አከበሩ።

 

የአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ በዕለቱ እንዳሉት የማርች 8 በዓል ሴቶች በማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን ጭቆና ተቋቁመው በፖለቲካው እና በምጣኔ ሃብቱ ያስመዘገቡት ውጤት የሚዘከርበት እና የሴቶችን ዕኩልነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች የሚሰሩበት ዕለት ነው ያሉ ሲሆን፣ በሀገራችን ባለፉት 50 ዓመታት ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀንን ምክንያት በማድረግ በሴቶች ላይ ያሉ ጫናዎችን፣ መብትና ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለማስቆም የተሰሩት ስራዎች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም መብትና ደህንነት ላይ ለውጥ እንዲመጣ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

 

በተለይም ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት የተሰሩ ስራዎች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በእጥፍ እንዲጨምር አድርገዋል ያሉት ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስተዳደሩም የተቋቋመበትን ተልዕኮ ለማሳካት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

 

በተቋሙ የሚገኘው የህጻናት ማቆያ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሴት ሠራተኞችን ጫና በመቀነስ በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያስቻለ ሲሆን፣ አስተዳደሩም የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴ በመከታተል እና አስፈላጊ ግብዓቶችም እንዲሟሉ በማድረግ በኩል በየወቅቱ ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

 

በዋናው መስሪያ ቤት በተከበረው በዚህ በዓል ላይ ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን በተመለከተ የውይይት ሠነድ የቀረበ ሲሆን፣ የጥያቄና መልስ ውድድርም ተካሂዷል። በተጨማሪም በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምንነትና መከላከያ መንገዶች ላይ ከባሻ ወልዴ ጤና ጣቢያ በመጡ የህክምና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል።

 

መጋቢት 04/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Share this Post