ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ሸጉ ኬሎ የዋስትና ህንጻዎች ምረቃ መረሃ-ግብር ላይ ያተላለፈ መልዕክት
ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ሸጉ ኬሎ የዋስትና ህንጻዎች ምረቃ መረሃ-ግብር ላይ ያተላለፈ መልዕክት
ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ፤ የኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ፤ የዕለቱ የክብር እንግዳ፤
ክቡራትና ክቡራን ሚኒስትሮች፤
ክቡር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክር ኢዮበ ተካልኝ፤
የተከበሩ አቶ ግርማ ብሩ የአስተዳደሩ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሰቢ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካር ሚኒስትር፤
የተከበራችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፤
የተከበራችሁ የአስተዳደሩ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት፤
ክቡራትና ክቡራን፤
በመጀመሪያ በዚህ ታሪካዊ ዕለት፤ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ለደረሰበት ውጤት ክብር ለመስጠትና የውጤቱ ተካፋይ ለመሆን በመካከላችን ስለተገኛችሁ፤ በራሴና በአስተዳደሩ ስም እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ።
ዛሬ የምንገኘው፤ የተቋሙ አዲስ ምዕራፍ በሚበሰርበትና የዓመታት የድካም ፍሬዎችን በምናይበት የደስታ ቀን ላይ ነው። እነዚህ ዛሬ የምናስመርቃቸው ዘመናዊ ሕንጻዎች ለተቋማችን ተራ የቁስ ሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ፤ ይልቁንም የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዋስትና ከነበረበት የህልውና ትግል ወጥቶ ወደ ስኬት ጎዳና መሸጋገሩን የሚያመላክቱ ሕያው አሻራዎቻችን ናቸው።
ክቡራትና ክቡራን፤
ተቋሙ ትላንት የነበረበትን ፈታኝ ሁኔታ መለስ ብሎ ማስታወስ፤ የዛሬውን ስኬት ትርጉም ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ ያደርገዋል። ለበርካታ ዓመታት የጡረታ ፈንዱ በከፍተኛ የመሸርሸር አደጋ ውስጥ ወድቆ፤ የነገው ዋስትና 'ይቀጥል ይሆን?' በሚል አጠራጣሪ ምዕራፍ ውስጥ አልፏል። ያ-ወቅት ተቋሙ ከነበረበት አስከፊ የቁልቁለት ጉዞ የተነሳ፤ ለመንግሥት ሠራተኞች የተስፋ ብልጭታ ያላሳየ፤ ለጡረታ ባለመብቶች ደግሞ ክብርንና መተማመንን ያልሰጠ ጭጋጋማ ጊዜ ነበር። ሆኖም በለውጡ መንግሥት ቁርጠኝነትና በወሰድናቸው የሪፎርም እርምጃዎች፤ ያ- ስጋት ዛሬ ወደ መልካም ዕድልና ብሩህ ተስፋ ተቀይሯል።
በተሻሻለው የጡረታ አዋጅና የመቋቋሚያ ደንብ በተገኘው ምቹ የሕግ ማዕቀፍ በመታገዝ፤ አስተዳደሩ ራሱን በጠንካራ የፋይናንስ መሠረት ላይ ለመገንባት እየታተረ ይገኛል። ተቋሙ የመገኘቱ ዋነኛ መሠረት ለሆኑት የጡረታ ባለመብቶች ተጠቃሚነት ሲል ሰፊ ርቀት ተጉዟል። ምንም እንኳን የጡረታ ባለመብቶች ብዛት በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 597,059 በ33 በመቶ ዕድገት በማሳየት 800,000 ቢደርስም፤ ከቁጥራዊ ዕድገቱ ባሻገር የባለመብቶችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ አምስት ጊዜ የጡረታ አበል ክፍያ ማስተካከያ አድርጓል። ይህም በ2010 ዓ.ም ብር 744.00 የነበረው ዝቅተኛ የጡረታ አበል ክፍያ ከአምስት እጥፍ በላይ ዕድገት በማሳየት ወደ ብር 4,669.00 እንዲደርስ ተደርጓል። ይሁን እንጂ አስተዳደሩ ይህም በቂ እንዳለሆነ ይገነዘባል።
የተከበራችሁ እንግዶች፤
አስተዳደሩ ፈንዱን ከመፍረስ ከመታደግ አልፎ አዋጭ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በመሰማራት በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ ችሏል። ዓመታዊ የጡረታ አበል ክፍያ አቅም በ2010 ዓ.ም ከነበረበት ብር 5.9 ቢሊዮን ከአምስት እጥፍ በላይ በማደግ ብር 36.5 ቢሊዮን ደርሷል። በእነዚህ ስምንት ዓመታት፤ ጠቅላላ የጡረታ ፈንዱም ከስድስት እጥፍ በላይ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ከዚህ ቀደም ከአንድ በመቶ በታች በሆነ የትርፍ ምጣኔ በአንድ መስክ ተወስኖ የነበረው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ዛሬ ወደ አምስት አዋጭ መስኮች እንዲሰፋ በመደረጉ፤ ዓመታዊ የኢንቨስትመንት ገቢያችን ከብር 591 ሚሊዮን ወደ ብር 40 ቢሊዮን ሊያድግ ችሏል። ይህም ተቋሙ የጡረታ አበል ክፍያ ወጪውን የመሸፈን ምጣኔ ከነበረበት 10 በመቶ ሙሉ በሙሉ ወደመሸፈን እንዲሸጋገር ለማድረግ አግዟል።
ዛሬ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በሐረር እና በጅማ ከተሞች የምናስመርቃቸው ባለግርማ ሞገስ የቅይጥ አገልግሎት ሕንጻዎች፤ ተቋሙ ዜሮ ሊባል ከሚችል ቋሚ ሀብት ድርሻ ተነስቶ በብር 30 ቢሊዮን የሚገመት ሀብት ለማፍራት አስችለዋል።
ወደፊት በምናደርገው ጉዞ፤ በግንባታውም ሆነ በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን የምንቀጥል ቢሆንም፤ ዋናው ትኩረታችን ተቋሙን በመላው ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የዘመነ፤ ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ ላይ ይሆናል። ይህንን ለማሳካትም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችንን በማፋጠን የጡረታ ባለመብቶች የሚገባቸውን ክብርና ዋስትና ያለ እንግልት ከቤታቸው ሆነው የሚያገኙበትን ወረቀት አልባ ሥርዓት እንገነባለን። ከዚህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጎን ለጎን ተቋማዊ አደረጃጀታችንን እና የሰው ኃይል አቅማችንን በወቅቱ ካለው ተወዳዳሪነት ጋር ለማጣጣም የሚያስችሉ ጥልቅ የሪፎርም ሥራዎችን ተግባራዊ እናደርጋለን። ይህም ዘመናዊ መሣሪያዎችን በዕውቀት፣ በታማኝነትና በላቀ የሥራ ሥነ-ምግባር የሚያንቀሳቅስ ብቁ የሰው ኃይልና ውጤታማ አሠራር በመፍጠር ህልማችንን ዕውን ያደርጋል።
በመጨረሻም፤
ለዚህ ስኬት መመዝገብ መሠረት ለሆናችሁ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፤ ስትራቴጂካዊ አመራር ለሰጣችሁ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና ለባለድርሻ አካላት ምስጋናዬ የላቀ ነው።
ይህ ስኬት እውን እንዲሆን፤ ርዕዩን ተጋርታችሁ ሌት ተቀን ስትደክሙ ለነበራችሁ የአስተዳደሩ አመራሮችና ሠራተኞች የላቀ አክብሮትና ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ሁሉንም ነገር በትዕግስትና በተስፋ ለጠበቃችሁ የጡረታ ባለመብቶች ደግሞ፤ "ይህ ድል የእናንተ ነው፤ ይህ ተቋም የእናንተ የክብር ማማ ነው!" ለማለት እወዳለሁ። ሁላችንም ያሉንን መልካም አጋጣሚዎች በጋራ በመጠቀም፤ ተቋማችንን የከፍታ፣ የጥራትና የክብር ተምሳሌት እናድርግ!
ለላቀ ለውጥ እንተጋለን!
አመሰግናለሁ!