አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው አንኳር ተግባራት

አስተዳደሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው አንኳር ተግባራት

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በተከናወኑ ተግባሮች አመቺ ባልነበሩ የፋይናንስ ተቋማት የጡረታ አበላቸውን ሲወስዱ የነበሩ 222 ሺ 47 ወይም ከዕቅዱ 99 በመቶ የጡረታ ባለመብቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ባንኮች የጡረታ አበላቸውን እንዲወስዱ ወደ ባንክ ተሸጋግረዋል። ይህም የጡረታ ባለመብቶችን ጉልበት፣ ጊዜና ወጪያቸውን እንዲቆጥቡ አስችሏቸዋል። እንዲሁም የተለያዩ መረጃ መስጫ መንገዶችን በመጠቀም ለ2,656,626 ተገልጋዮች አስተዳደሩ ስለሚሰጠው አገልግሎት፣ አሠራር ስለጡረታ አዋጁና የማስፈጸሚያ መመሪያ እንዲሁም የጡረታ ባለመብቶች መብቶቻቸውን እንዴት ማስከበር፣ ለማስከበር ደግሞ ምን ምን ማሟላት እና ግዴታቸውን እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ወ.ዘ.ተ መረጃ ተሰጥቷል።  

ሌላው የምዝገባና የአበል ውሳኔ አገልግሎትን ከማሳደግ አንጻር ለ110,653 (የዕቅዱን 92 በመቶ) አዳዲስ የመንግስት ሠራተኞች የጡረታ መለያ ቁጥር ተሰጥቷል። በተጨማሪም ለ29,948 አዳዲስ የጡረታ ባለመብቶች ወደ ጡረታ እንዲሸጋገሩ ተደርጎ የጡረታ አበል ተወስኖላቸው አበላቸውን እንዲያገኙ ተደርጓል። ለ101,429 ተገልጋዮች ደግሞ ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ማለትም ውክልና፣ አድራሻ ለውጥ፣ የውዝፍ አበል ክፍያ እና መታወቂያ ዕድሳት የመሳሰሉ አገልግሎቶች መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ በጥቅሉ ብር 28 ነጥብ 33 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ ብር 26 ነጥብ 47 ቢሊዮን ወይም የዕቅዱን 93 በመቶ ገቢ ተሰብስቧል። ከዕቅዱ አኳያ ሰባት በመቶ ጉድለት አሳይቷል። ይህም ያልተሰበሰበው ገቢ በገንዘብ ሲሰላ 1.8 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው። ስለዚህ ያልተሰበሰበው ብር ትልቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአገሪቱ ባለው የጸጥታ ጉድለት ሳቢያ ሙሉ ለሙሉ በትግራይ ክልል እና በወረራ ተይዘው በነበሩ የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልሎች አካባቢ የጡረታ መዋጮ ገቢ ባለመሰብሰቡ ነው። እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ጉድለት ሳቢያ የሰበሰቡትን የጡረታ መዋጮ ገንዘብ አሟጠው ወደ ጡረታ ፈንዱ የማያስገቡ መስሪያቤቶች በመኖራቸው ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ። 

በአራት አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በመሳተፍ ብር 5.57 ቢሊዮን ለማግኘት ታቅዶ 7.22 ቢሊየን ብር (የዕቅዱን 130 በመቶ) ገቢ ተገኝቷል፤ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንጻር ከፍ ሊል የቻለው አዋጭ የኢንቨስትመንት መስኮች ወይም ዘርፎች በመስፋታቸው ነው። ሆኖም ከኢንቨስትመንቱ የተገኝው ገቢ ትልቅ ቢሆንም ከወቅታዊው የገንዘብ ግሽበት ጋር ሲነጻጸር ገቢው ግሽበቱን የሚሸፍን ባለመሆኑ የጡረታ ፈንዱ ዘላቂነት ላይ ስጋት ይኖረዋል። ስለዚህ በቀጣይ የበጀት ዓመት ላይ ከኢንቨስትመንት የሚገኝው ገቢ የዋጋ ግሽበቱን ተቋቁሞ እራሱን የሚችልበት ሥራዎችን መሥራት ይጠይቃል። 

ሆኖም በጥቅሉ ከጡረታ መዋጮና ኢንቨስትመንት ወደ 36 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥ ለጡረታ አበል 8 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ 7.28 ቢሊዮን ብር ለጡረታ ባለመብቶች ክፍያ ተፈጽሟል። በዚህም ትክክለኛና የሚገባቸው የጡረታ ባለመብቶች ብቻ አበል እንዲያገኙ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ በማከናወን ለጡረታ ባለመብቱ ለመክፈል ከታቀደው የዘጠኝ በመቶ ቅናሽ ማስመዝገብ ተችሏል። እንዲሁም ለመደበኛና ለፕሮጀክት በጀት 957.69 ሚሊየን ብር ሥራ ላይ መዋሉንም ጠቁመዋል።  

የውስጥ ቁጥጥርና የተጠያቂነት አሠራርን ከማስፈን አኳያ ደግሞ የተቋሙን አዋጅ፣ ማቋቋሚያ ደንብ እና የሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ በማዘጋጀት አዋጁን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፀደቅ ተችሏል። በዚህም ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 መጋቢት 08 ቀን 2014 በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ወጥቶ ሥራ ላይ ውሏል። አዋጁ ሥራ ላይ በመዋሉ በተለይ ከጡረታ መዋጮ ገቢ ጋር በተያያዘ የመስሪያቤቱን የቁጥጥርና የማስፈጸም አቅም አጠናክሮታል። ያልተሰበሰቡ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ አቅም ይፈጥራል፤ ፈጥሯልም። በአንጻሩ የተቋሙ የመቋቋሚያ ደንብ ተጠናቆ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ እየታየ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ባለመጽደቁ መመሪያዎቹ ተዘጋጅተው ወደ ተግባር አልገቡም። ስለዚህ የሪፎርም ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም ማለት ይቻላል።

በተጨማሪም የጡረታ መዋጮ ገቢ ትክክለኝነት ለማረጋገጥ በመላ አገሪቱ ባሉ የጡረታ መዋጮ በሚሰበስቡ መስሪያቤቶች ላይ የምርመራ ሥራ ይከናወናል። ከዚህ አኳያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 3,106 መስሪያቤቶችን በመመርመር 2.27 ቢሊዮን ብር በ2013 ወደ ጡረታ ፈንዱ መግባት የነበረበት ነገር ግን ያልገባ ገቢ ተገኝቷል። ከዚህ ውስጥ ወደ 995 ሚሊዮን ብር ከመስሪያቤቶች ጋር በአስተዳደራዊ መንገድ ግንኙነት በመፍጠር ገቢ ማድረግ ተችሏል። እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ እርምጃ ተወስዶ ከሂሳብ አካውንታቸው ተቆርጦ ወደ ጡረታ ፈንዱ ገቢ ተደርጓል። ሌሎች ደግሞ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ አሉ። በዚህም በ2013 እና ከዛ በፊት በነበሩ ዓመታት እንዲሁም የዘንድሮን ጨምሮ በጥቅሉ በወቅቱ ያልገባ 2.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስደረግ ተችሏል። ነገር ግን ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር አሁንም በወቅቱ ወደ ጡረታ ፈንዱ ያልገባ ውዝፍ ገንዘብ አለ። ይህንን ውዝፍ ገንዘብ በቀጣይ አሟጦ ገቢ የማስደረግ ስራ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 13/2014

Share this Post