የመንግሥት ሠራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና አስተዳደር ወጣት ሠራተኞች በዲጂታል ዘመን ዝግጁነት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ወሰዱ
አዲስ አበባ — የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ለወጣት ሠራተኞቹ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለመጪው ዲጂታል አለም ዕድል ማብቃት (Empowering Ethiopia's Youth for the Digital Future) በሚል አርዕስት የማነቃቂያ ሥልጠና ሰጠ። ሥልጠናው “ስለ 2030 የኢትዮጵያ ዲጂታል ጉዞ፣ ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና አለም በቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የደረሰበትን የሚያሳዩ እና እያንዳንዱን ወጣት ሠራተኛ ለአገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ዝግጁ ለማድረግ ያለመ ነው።
በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሸጉ ኬሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ቴክኖሎጂን መላመድና አዳዲስ ክህሎቶችን ማዳበር የአንድ ወቅት ምርጫ ሳይሆን የዘመኑ ግዴታ መሆኑን ያሳሰቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ሥልጠናው አስተዳደሩ የሚሰጣቸውን የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎቶች ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እና ፍትሃዊ ለማድረግ ለሚከናወነው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል። አቶ ሸጉ አክለውም “ወጣት ሠራተኞቻችን እዚህ ያገኛችሁትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር፣ የአገራችንን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትና የተቋማችንን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለማርካት በቁርጠኝነት እንድትሠሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
ይህ ሥልጠና በዋናነት ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይበልጥ ዘመናዊና ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እንዲሁም ወጣት ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየመጡ ያሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ክህሎቶችንና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አጠቃቀምን ተረድተው ለተቋማዊና አገራዊ ዕድገት እንዲተገብሩት ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በሥልጠናው ወቅት ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚችሉባቸው የርቀት የሥራ መስመሮች እና ራሳቸውን ለወደፊቱ የሥራ ዓለም እንዴት ማዘጋጀት እንዳለባቸው ሰፊ ግንዛቤ ተሰጥቷቸዋል።
አስተዳደሩ አገልግሎቶቹን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመቀየር በርካታ ሪፎርሞችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ የሰው ኃይልን በተለይም ወጣቱን ክፍል በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ማብቃት ለዚሁ ስኬት ወሳኝ መሆኑን አስታውቋል። በሥልጠናው የተሳተፉ ወጣት ሠራተኞችም የተሰጣቸው ሥልጠና ተነሳሽነታቸውን ያሳደገ እና ለቀጣይ የዲጂታል ሥራዎች አዲስ እይታ የፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።