ከምርጫ ድል ማግስት፣ ጠንካራ መንግስት በሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ

ከምርጫ ድል ማግስት፣ ጠንካራ መንግስት በሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ
=======//=========
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር “ከምርጫ ድል ማግስት፣ ጠንካራ መንግስት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ከአስተዳደሩ ሠራተኞችና የስራ ኃላፊዎች ጋር ሰኔ 12/2018 ውይይት ተካሄደ።
 
የውይይት ሰነዱን ያቀረቡት የአስተዳደሩ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት የሰነዱ ዓላማ የድህረ ምርጫ ስራዎችን በውጤታማነት በመፈጸም ጠንካራ መንግስት የመመስረት ግባችንን በተሟላ ሁኔታ ለማሳካት ያለመ ነው።
 
በመድረኩ ላይ በውይይቱ አስፈላጊነት፣ በድህረ ምርጫ ወቅት ዕሳቤያዊ መላምቶች፣ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ አፈጻጸምና በድህረ ምርጫ ስራ የሚኖረው ፋይዳ በሚሉ እና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል። በድህረ ምርጫ ስራዎችም የእስካሁኑን የምርጫ ስራዎች በጥልቀት መገምገምና መሰነድ፣ በድህረ ምርጫ ስራዎች አንድምታና የአፈጻጸም ስልቶች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ የምርጫ ውጤት ቅቡልነትን የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራት፣ መደበኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በስነ ምግባርና በውጤታማነት ማስቀጠል እንዲሁም በድህረ ምርጫ ወቅት የመንግስት ሠራተኞችን ዲሲፕሊን ማረጋገጥ የሚሉና ሌሎችም ሀሳቦች ተነስተዋል።
 
በውይይት መድረኩ ላይ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በድል እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸናፊነቱን አስመስክሯል። ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ ድምጽ የሰጠው ህዝብ መካስ አለበት። ሕግና ስርዓትን በማክበር ከፖለቲካዊ አድልዖ የፀዳ አገልግሎት መስጠትም ይገባል።
 
በምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት አሸናፊ ፓርቲ በይፋ ተገለጾ መንግስት እስከሚመሰረት ድረስ የመንግስት ሠራተኛው ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ከሌላው ጊዜ በተለየ ጠንክሮ መስራት ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፣ የአስተዳደሩ ሠራተኞችና የስራ ኃላፊዎችም ተገልጋዮችን በአግባቡ በማስተናገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሏል።
 
በክረምት ወቅትም የአረንጓዴ አሻራ እና የማህበራዊ ድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ በመሆኑ ሁላችንም በትብብር ልንሰራ ይገባል።
 
በዕለቱ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የዋና መ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የመሀል ሪጅን እና አዲስ አበባ ሪጅን ጽ/ቤት ሠራተኞችም ተካፍለዋል።

Share this Post