አስተዳደሩ የዕውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር አካሄደ
አስተዳደሩ የዕውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብር አካሄደ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ያስመዘገበውን ስኬት አስመልክቶ ግንቦት 12/2018 ለሠራተኞቹ የምስጋና እና ዕውቅና የመስጠት መርሃ ግብር አካሄደ።
በዚህ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሸጉ ኬሎ እንዳሉት ተቋሙ በተለያዩ ከተሞች ያስገነባቸውን ስምንት ዘመናዊ የቢሮና የንግድ ሕንጻዎች ግንባታ አጠናቆ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ማስመረቁ በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በትጋት በማከናወናቸው የተገኘ ውጤት በመሆኑ ሁላችሁም ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ወደፊትም እንዲህ አይነት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ በመሆኑ አሁንም መደጋገፍን መሠረት በማድረግ በአንድነትና በጋራ ሆነን የተቋሙን ስኬት ማስቀጠል ይጠበወቅብናል ብለዋል።
አስተዳደሩ በዋናነት የተቋሙን የመፈጸም አቅም በማሳደግ የመንግሥት አገልግሎት ጡረታ ዐቅድን የማጠናከርና የማስፋት፤ የኢንቨስትመንት ፈንዱን በማዳበር የጡረታ ባለመብቶችን ገቢ በየጊዜው የማሻሻል እና በፈንድ አስተዳደር ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቁርጠኝነት በመቅረፍ የጡረታ ፈንዱን ቀጣይነትና አስተማማኝነት የማረጋገጥ ኃላፊነቶች በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ተቀምጠውለታል። በመሆኑም እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካትና የጡረታ ባለመብቶችን ህይወት ለመለወጥ በትብብር በመስራት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የላቀ አገልግሎት የሚሰጥ ጠንካራ ተቋም ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በዚህ መርሃ ግብር ላይ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አስተዳደሩን በኃላፊነት በመምራት አሁን ለደረሰበት ስኬት እንዲበቃ በማድረግ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳባ ኦሪያ ምስጋና እና ዕውቅና የመስጠት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።
በዋና መ/ቤት በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የአስተዳደሩ አመራሮች፣ የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባና የመሃል ሪጅን ጽ/ቤት ሠራተኞች ተካፍለዋል።