የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት በይፋ ተመረቀ

የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት በይፋ ተመረቀ

==========//=========

የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጬ ክ/ከተማ በቱሉዲምቱ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተግበራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ዛሬ ጥር 02/2018 ዓ.ም በይፋ ተመረቀ፡፡

በምረቃው ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳባ ኦርያ እንዳሉት የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የወተት ላሞችን በማርባት ለተማሪዎች የምገባ አቅርቦትን ለማሻሻል እና ከፕሮጀክቱ የሚገኘውን ገቢ ለትምህርት ቤቱ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ እንዲውል መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም ዛሬ የተመረቀው የወተት ላሞች ዕርባታ ፕሮጀክት የተማሪዎችን ምገባ ከማገዝ ባሻገር ለገበያ በማዋል ለት/ቤቱ ገቢ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብም የወተት አቅርቦት እንዲሟላ በማድረግ ረገድ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ይደግፋል ብለዋል።

በት/ቤቱ ውስጥ ተግባራዊ የተደረገው ይህ የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክት ፋይናን ያደረጉት አካላት ከአስተዳደሩ ጋር የሚሰሩ የፋይናንስ ተቋማት መሆኑን ገልፀው የተገዙት ላሞች በወተት ምርታማነታቸው የተመረጡ፣ ሙሉ ጤንነታቸው የተረጋገጡ የወተት ላሞች መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም ለላሞቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና የሰው ሃይልም ጭምር እንደተሟላላቸውም ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ካሳሁን ገላና በበኩላቸው እንደገለጹት አስተዳደሩ አጋር አካላትን በማስተባበር በተግባር ያሳየው ሥራ ለሁሉም ተቋማት ምሳሌ የሚሆን እና ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አመስግነው ቀጣይ መሰራት ያለባቸውን ሥራዎች አመላክተዋል፡፡

በምረቃው ላይ የሸገር ከተማ አመራሮች፣ የኮዬ ፈጬ ክ/ከተማ አመራሮች፣ የአስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም የትምህርት ቤቱ መምህራን እና ተማርዎች የተገኙ ሲሆን በምረቃው ጎን ለጎን በክረምት ወራት የተተከሉትን ችግኞች ውሃ የማጠጣት ሥራ ተከናውነዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ለማድረግ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርከቶላቸዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ለማድረግ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም የመሰረተ ድንጋይ መኖሩ የሚታወስ ነው፡፡

 

://****

ጥር 02/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Share this Post