የአስተዳደሩ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በወፍ በረር ሲቃኝ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ከያዘው ዕቅድ አንጻር የተቋሙ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ምን እንደሚመስል በአስተዳደሩ የዕቅድ፣ ጥናትና ሪፎርም ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ማናዬ ጋር እንደሚከተለው ቆይታ አድርገናል።

የተቋሙን የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ተቋሙ ያስቀመጠውን የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ እቅዶችን ለማሳካት ልዩ ልዩ ግቦችን ነድፎ እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም የጡረታ ባለመብቶች ከጤናና ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ እንግልትና ድካም እንዳይደርስባቸው እንዲሁም የተሻለ አገልግሎት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ለማስቻል ከባንኮች ጋር የተጀመረውን ስራ በማጠናከር ባለፉት ስድስት ወራት 220 ሺህ የጡረታ ባለመብቶች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ባንኮች የጡረታ አበላቸውን እንዲወስዱ ወደ ባንክ ተሸጋግረዋል። እንዲሁም አሁን ላይ ከባንክ ውጭ ባሉ ሌሎች ተቋማት የጡረታ አበላቸውን የሚወስዱ 4 ሺህ 100 ገደማ የጡረታ ባለመብቶች ብቻ ናቸው። እነዚህን የቀሩትን የጡረታ ባለመብቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠቃሎ በባንክ ክፍያ ውስጥ ለማስገባት እቅድ ተይዞ በትጋት እየተሰራ ይገኛል።

ሌላው ተገልጋዮች መብቶቻቸውን እንዴት ማስከበር፣ ለማስከበር ደግሞ ምን ምን ማሟላት እና ግዴታቸውን እንዴት መወጣት እንዳለባቸው ወ.ዘ.ተ ተቋሙ መረጃዎችን ለተገልጋዮች መስጠት ይጠበቅበታል። ከዚህ አንጻር ባለፉት ስድስት ወራት ለአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ተገልጋዮች መረጃ ማድረስ ተችሏል። ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር ማሳካት የተቻለው 74 በመቶ ሲሆን፤ አፈጻጸሙ ዝቅ ያለበት ምክንያት በሬዲዮ ለተገልጋዮች ሲተላለፍ የነበረው ፕሮግራም ዘግይቶ በመጀመሩ ነው።        

በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት 75ሺህ አዳዲስ የመንግስት ሠራተኞችን ለመመዝገብ ታቅዶ 73 ሺህ 300 ሠራተኞች ተመዝግበዋል። ይህም የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፤ ከተያዘው ዕቅድ አኳያ ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ያልተቻለው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ባለው አለመረጋጋት በስራ ላይ የሌሉ ጽህፈት ቤቶች (የሰሜን ሪጅን ጽህፈት ቤቶች /የትግራይ ክልል) በመኖራቸው ነው። ስለዚህ በዚህ አካባቢ መመዝገብ የነበረባቸው ሠራተኞች ባለመመዝገባቸው ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አልተቻለም። ከአበል ውሳኔ ጋር በተያያዘ በስድስት ወራት ውስጥ 16 ሺህ አዳዲስ የጡረታ ባለመብቶችን ተቀብሎ ወደ ጡረታ ለማሸጋገር ታቅዶ፣ 19 ሺህ አዳዲስ የጡረታ ባለመብቶችን የጡረታ ተጠቃሚ በማድረግ ከታቀደው እቅድ በላይ ማሳከት የተቻለ ሲሆን፣ በተጨማሪም 74ሺህ 893 የጡረታ ባለመብቶች የአድራሻ ለውጥ፣ ውክልና የመስጠትና የጡረታ መታወቂያ እድሳት የመሳሰሉ አግልግሎቶችን ባለፉት ስድስት ወራት አግኝተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 21 ቢሊዮን ብር የጡረታ መዋጮ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል። አፈጻጸሙም 94 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ3.82 ቢሊየን ብር ብልጫ አሳይቷል፤ ከከበጀት ዓመቱ ዕቅድ አንጻር ጉድለት ያሳየበት ምክንያት በአገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተወሰኑ ጽህፈት ቤቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ከስራ እንቅስቃሴ ውጭ በመሆናቸውና በአንዳንድ ክልሎች የጡረታ መዋጮ በአግባቡ ባለመሰብሰቡ ነው።   

የጡረታ ፈንዱን ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል አስተማማኝነቱንና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ከክፍያ ተራፊውን የፈንድ ገንዘብ ወደ ኢንቨስትመንት በማሰማራት ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኝት ታቅዶ፣ አራት ነጥብ 66 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። ይህ አፈጻጸም ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ1.98 ቢሊየን ብር ገቢ በብልጫ ተገኝቷል፡፡ ከዕቅድ በላይ ገቢ ማግኝት የተቻለውም የኢንቨስትመንት መስኮችን በማስፋትና የአመራሩ ጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

በሌላ በኩል በስድስት ወር ውስጥ ወደ አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የጡረታ አበል ክፍያ ለመፈጸም ታቅዶ ለ642 ሺህ የጡረታ ባለመብቶች አራት ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል። ክፍያው ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከዚህ አኳያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ካለው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የጡረታ አበል ክፍያ ያልተፈጸመላቸው የጡረታ ባለመብቶች አሉ። ነገር ግን መረጃዎች ተደራጅተው ስለተቀመጡ የጡረታ አበላቸውን ያልወሰዱ የጡረታ ባለመብቶች በጠየቁበት ጊዜ የጡረታ አበላቸውን እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

በስድስት ወራት ውስጥ ሁለት ሺህ 400 የመንግስት መስሪያ ቤቶች የጡረታ መዋጮን በአግባቡ ገቢ ስለማድረጋቸው ለማረጋገጥ ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ ሁለት ሺህ 235 መስሪያ ቤቶችን ኦዲት በማድረግ ሁለት ነጥብ ስድት ቢሊዮን ብር መግባት የነበረበት የጡረታ መዋጮ ሳይገባ ተገኝቷል። ይህንን አለማስገባታቸውን ከመስሪያ ቤቶቹ ጋር መተማመኛ ከመፈራረም ባሻገር በኦዲት ግኝቱ ሳይገባ ከቆየው ገንዘብ ውስጥ ከ698 ሚሊየን ብር በላይ መሠብሰብ ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 100 ሚሊዮን ብር በህግ አግባብ(በፍርድ ቤት ክርክር) መሰብሰብ ተችሏል። ነገር ግን በመስሪያ ቤቶቹ ከተገኝው ውዝፍ እዳ አንጻር የተሰበሰበው ገቢ ዝቅተኛ ነው።  ስለዚህ ውዝፍ እዳቸውን ያልከፈሉ ተቋማት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እየተወሰደ ነው። ወደ ፊትም ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ ባልተወጡ በተለይ የመስሪያ ቤቱና የፋይናንስ ኃላፊዎችን በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ ይፈጠራል ብለዋል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መጋቢት 5/2014

Share this Post