የአስተዳደሩ አመራሮች እና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሄዱ

የአስተዳደሩ አመራሮች እና ሠራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሄዱ

/PSSSA/ ሐምሌ 26/2016

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አመራሮች እና ሠራተኞች በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አከናወኑ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት አስተዳደሩ ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን ሰፊ የማህበራዊ ድጋፍ ተሳትፎ ሲያከናውን የቆየ መሆኑን ገልጸው በተለይ በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ ከአስር ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለ8 አቅመ ደካሞችና ጡረተኞች የሚሆን ሕንጻ አስገንብቶ አስረክቧል ብለዋል። አክለውም የዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም የዚሁ የማህበራዊ ድጋፍ ተሳትፎ አካል ሲሆን፣ ለወደፊቱም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ አስተዳደሩ በዕቅዱ መሠረትም ችግኞቹን የመንከባከብ ስራ ያካሂዳል ብለዋል።

የልደታ ክ/ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሄለን ጥበቡ በበኩላቸው አስተዳደሩ በክ/ከተማው ችግኝ የመትከል ስራ በማከናወኑ አመስግነው ወቅቱን ጠብቆ የመንከባከብ ስራዎችንም በጋራ እናከናውናለን ብለዋል።

በዕለቱ በልደታ ክፍለ ወረዳ 05 በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የተቋሙ አመራሮች፣ የዋናው መ/ቤት እና የመሀል ሪጅን ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የክ/ከተማውና የወረዳው የአረንጓዴ ልማት ጽ/ቤት ሠራተኞች ተካፍለዋል።

Share this Post