በልማት ባንክ በኩል ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

 

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ከሰኔ 27 እስከ ሐምሌ 01 /2015 ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ምደባ ላላገኙ ሠራተኞች በቢሾፍቱ ከተማ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ሐምሌ 01 ቀን 2015 ተጠናቀቀ፡፡

በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞች በተካፈሉበት በዚህ የስልጠና መርሃ ግብር ላይ ሠራተኞችን ለስራ የሚያዘጋጁ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን፣ በስልጠናው ማጠናቀቂያም ሠራተኞች በቀጥታ ወደ ስራ ለመግባት እና በአንድ ማዕከል ለመደራጀት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችን ለማከናወን ተወካዮች መምረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በስልጠናው ማብቂያ ላይ ከመድረክ እንደተገለጸው ተቋሙ ለሠራተኞቹ የንግድ ስራ ዕቅድ/ Business Plan/ የማስጠናት፣ የንግድ ፈቃድ እንዲያገኙ የመደገፍ እና ስራ ለመጀመር የሚያስፈልጉ ሌሎችም ተያያዥ ስራዎችን ያከናውናል የተባለ ሲሆን፣ የተደራጁ ሠራተኞችም ወደ ስራ ገብተው አስኪጠናከሩ ድረስ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ተብሏል።

ተሳታፊ ሠራተኞች በሰጡት አስተያየትም ተወካዮቻቸው በሚመርጡት የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በተሰጡ ስልጠናዎች በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን እንዲሁም በአንድ ማዕከል በመደራጀት ለመስራት መወሰናቸውን በፊርማቸው ገልጸዋል።

ሐምሌ 01 ቀን 2015 በተጠናቀቀውና ለአምስት ተከታታይ ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ሲሰጥ በቆየው በዚህ የስልጠና መድረክ ከዋናው መስሪያ ቤት፣ ከሪጅን እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የመጡ እና ስልጠናውን በመውሰድ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለመደራጀት ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞች ተካፍለዋል፡፡

Share this Post