አስተዳደሩ የለማ ሶፍትዌር ግዢ እና በዳታ ሴንተር ግንባታ ላይ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር የስራ ማስጀመሪያ ምክክር አካሄደ

አስተዳደሩ የለማ ሶፍትዌር ግዢ እና በዳታ ሴንተር ግንባታ ላይ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር የስራ ማስጀመሪያ ምክክር አካሄደ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የተቋሙ የአይ.ቲ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የለማ መተግበሪያ ሶፍትዌር ግዢና ማላመድ(Customization) እና የዳታ ሴንተር ግንባታ ላይ የማማከር እና ሌሎች ስራዎችም ላይ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር ታህሳስ 06 ቀን 2015 በካፒታል ሆቴል የስራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ እንደተገለጸው አስተዳደሩ ስራዎቹን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችለው የኔትዎርክ ዝርጋታ፣ ዲጂታይዜሽን፣ የሶፍትዌር ልማት እና የዳታ ሴንተር ግንባታን ያቀፈ የአይ.ቲ ፕሮጀክት ቀርጾ ላለፉት አራት ዓመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

የአይ.ቲ ፕሮጀክቱ አካል ከሆኑት ውስጥ የኔትዎርክ ዝርጋታ እና ከ2.8 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሠራተኞችንና ከ700 ሺህ በላይ ጡረተኞችን ፋይል ወደ ዲጂታል ቅርጽ መቀየር (ዲጂታይዜሽን) ስራዎች ተጠናቀው አግልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር በተገባው ውል  መሠረት በለማ ሶፍትዌር ግዢ እና በዳታ ሴንተር ግንባታ ላይ በዩኒቨርስቲው በተዘጋጀው የድርጊት መርሃ ግብር መሠረት ስራዎች እንዲጀመሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በስራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ እና የዩኒቨርስቲው አመራሮች እንደገለጹት ስራዎቹን በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት እንዲከናወኑ በየወቅቱ በመገናኘት ስራዎቹ የደረሱበትን ደረጃ በጋራ እንደሚገመግሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ዩኒቨርስቲውም በየወቅቱ ስራዎቹን በተመለከተ ሪፖርት ያቀርባል ተብሏል፡፡

አስተዳደሩ አሠራሩን ለማዘመን በዕቅድ ይዞ ከሚንቀሳቀስባቸው ተግባሮች መካከል ዋናው እና ግንባር ቀደሙ ይህ የአይቲ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት በፊትም የአስተዳደሩን አሥር ሪጅን ጽ/ቤቶች እና ሃምሳ ዘጠኝ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከዋናው መ/ቤት ጋር ዘመናዊ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖራቸው ያደረገ የኔትዎርክ ዝርጋታ ተከናውኖ በአገልግሎት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የዲጂታይዜሽን ስራውም የተጠናቀቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር የተጀመረው የለማ ሶፍትዌር ግዢ እና የዳታ ሴንተር ግንባታም የአይ.ቲ ፕሮጀክቱ አካል መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Share this Post