አስተዳደሩ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አደረገ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ለሁለት የመንግሰት ትምህርት ቤቶች ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ህዳር 15/2015 ድጋፍ አደረገ።

የርክክብ ስነ-ስርዓቱ በተከናወነበት ዕለት የተገኙት የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት ተቋሙ በተለያዩ የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ በርካታ ተግባሮችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለትምህርት ቤቶቹ የሚደረገው ይህ ድጋፍም በስራቸው ላይ የሚታየውን የቁሳቁስ እጥረት በተወሰነ መልኩ በመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው። ትምህርት ቤቶች ወደፊት አገርን የሚረከቡ ዜጎች በዕውቀት የሚታነጹበት ቦታ በመሆኑ አስተዳደሩ ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት ለትምህርት ቤቶቹ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለየካ ጣፎ አንደኛ ደረጃ እና ለእድገት ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በአጠቃላይ ግምታዊ ዋጋቸው ሁለት መቶ ሺህ ብር የሆኑ ኮምፒዩተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ የፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ ወንበሮች ጠረጴዛዎች እና ሌሎችም ድጋፎች ተደርገዋል፡፡

በዕለቱም በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ በአስተዳደሩ በኩል ተተክለው የነበሩ ችግኞችን የመንከባከብ እና ውሃ የማጠጣት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በአስተዳደሩ በኩል የተደረገላቸውን ድጋፍ አስመልክቶ የትምህርት ቤቶቹ የስራ ኃላፊዎች፣ መምህራን እና የወላጆች ተወካዮች በሰጡት አስተያየት ድጋፍ የተደረጉላቸው ቁሳቁሶች ለስራቸው ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉላቸው ከመሆኑም ባሻገር አስካሁን የነበሩባቸውን ችግሮች በአብዛኛው መቅረፍ ያስቻሉ በመሆናቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የውሃ፣ የላቦራቶሪ እንዲሁም የሚታመሙ ተማሪዎችን ወደ ህክምና ተቋማት ለማድረስ የተሽከርካሪ እጥረት ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Share this Post