የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ተከበረ

የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ተከበረ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አመራሮች እና ሠራተኞች 35ኛውን የአለም ኤድስ ቀንን ‹‹ፍትሐዊና ተደራሽ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አገልግሎት!›› በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 30/2015 አከበሩ፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን በቀለ በበዓሉ ዕለት እንዳሉት የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ መሆኑን የሚያሳዩ አሃዛዊ መረጃዎች ቢኖሩም፣ ውጤቱ ግን ዝቅተኛ በመሆኑ አሁንም የማኀበረሰብ የጤና ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም እየታየ ያለው መዘናጋት እና ቸልተኝነት ዋጋ እያስከፈለን በመሆኑ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማስቀጠል ይገባል፡፡ አስተዳደሩም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ጉዳይን በዕቅዱ ውስጥ በማካተትና በዘርፉም የአመራሩን እና የሠራተኛውን ግንዛቤ ለማሳደግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ ከሠራተኞች በሚሰባሰብ መዋጮም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፈንድ በማቋቋም ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝ ሠራተኞች በየወሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ‹‹ሴትን አከብራለሁ፤ ጥቃቷንም እከላከላለሁ!›› በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ የተከበረው የፀረ-ጾታ ጥቃት ቀን በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጾታዊ ጥቃት በመከላከልና ሴቶችን በማክበር በኩልም እኛ ወንዶች ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን ያሉ ሲሆን፣ በስርዓተ ጾታ ጉዳይ ላይ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶችን በማስወገድ አጋርነታችንን በተግባር ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በዕለቱም ከጋንዲ ሆስፒታል በመጡ የሕክምና ባለሙያዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ በጡት ካንሰር እና በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምንነት እና መከላከያ መንገዶች ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

Share this Post