18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በድምቀት ተከበረ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር አመራሮችና ሠራተኞች 18ኛውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብስራት፣ ለብሄራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ!” በሚል መሪ ሃሳብ ጥቅምት 3/2018 በድምቀት አከበሩ።

በበዓሉ አከባበር ላይ የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳባ ኦርያ፣ ሠንደቅ ዓላማ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ፤ ዜጎች አገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜታቸውን የሚገልፁበት፤ ታሪካዊ ትስስርና ስነ-ልቦናዊ አንድነት የሚንፀባረቅበት የአንድነትና ህብረት ዓርማና ምልክት ነው ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ ጊዜያት ጠላቶቻቸው የሚከፍቱባቸውን ዘመቻ በመመከት በሀገራቸው ነጻነትና ክብር የማይደራደሩ መሆኑን በማስመስከር የጠላቶቻቸውን ህልም ማምከን በመቻላቸው ሀገራችንን ዕውነተኛና ዘላቂ የነጻነት ምድር አድርጓታል ብለዋል፡፡ ዋና ስራ አስፋጻሚው አክለውም የዘንድሮውን የሠንደቅ ዓላማ ቀን የምናከብረው በተለያዩ ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎች ውስጥ ሆነን ቢሆንም እንኳን በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በተሰሩ ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች እንደ ሀገር አመርቂ ውጤት እያስመዘገብን ባለንበት ወቅት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። በዋናነትም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁ፣ የተፈጥሮ ጋዝ በማውጣት ጥቅም ላይ ማዋል መጀመሩ እንዲሁም የባህር በር ጉዳይን አለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ መቻሉ የስኬታችን ማሳያዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

በዕለቱም ከሠንደቅ ዓላማ ክብር ጋር በተያያዘ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በውይይት መድረኩ ላይ እንደተገለጸው የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን የገባነውን ቃልኪዳን የምናድስበት፣ አንድነታችንን የምናጠናክርበት እና የተሰጠንን ተልዕኮ በአግባቡ እና በብቃት በመወጣት ልናከብረው ይገባል ተብሏል።

18ኛው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በዋናው መ/ቤት፣ በሪጅኖች እና በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችም ጭምር በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት የተከበረ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

Share this Post