አስተዳደሩ የ2016 ዕቅድ አፈጻጸሙን ገመገመ
አስተዳደሩ የ2016 ዕቅድ አፈጻጸሙን ገመገመ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሙን ከሐምሌ 8 እስከ ሐምሌ 12 ቀን በሀዋሳ ከተማ በማካሄድ አጠናቀቀ።
በዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ላይ በቀረበው ሪፖርት እንደተገለጸው ለ149,251 የመንግስት ሠራተኞች የጡረታ መለያ ቁጥር ተሰጥቷል፤ ለ68,388 የጡረታ ባለመብቶች የጡረታ አበል ተወስኗል፤ በተለያዩ የመረጃ መስጫ መንገዶች ለ1.7 ሚሊየን ተገልጋዮች መረጃ ተሰራጭቷል፤ ከ3424 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለተሳተፉ 10,401 ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተስጥቷል፤ 52.9 ቢሊየን ብር የጡረታ መዋጮ ተሰብስቧል፤
ለጡረታ አበል ክፍያ ብር 21.2 ቢሊየን ተላልፏል፤ የሪፎርም፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን በተመለከተም የሠራተኞች አስተዳደር፣ የስነ ምግባር የፋይናንስ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ገቢ አፈጻጸምና የግዢ መመሪያ ጸድቆ ተግባራዊ ሆኗል፤ በ3,739 መስሪያ ቤቶች ላይ የጡረታ መዋጮ ምርመራ ተደርጓል፤ የ741 ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃ በማጣራት ትክክለኛነቱ ተረጋግጧል፤ የሙስና ቅድመ መከላከልን ለማጠናከር 217 ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ አድርገዋል የተባለ ሲሆን፣ የተቋሙን የማህበራዊ ተሳትፎ በማጠናከርም ለሸገር ከተማ አስተዳደርና በሲዳማ ክልል ለይርጋለም ከተማ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ብር 3.5 ሚሊየን፣ ለተተኪ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ማሟያ ብር 117,895 ድጋፍ ተደርጓል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በመድረኩ ላይ የ2017 ዕቅድ ለውይይት የቀረበ ሲሆን፣ የትኩረት ጉዳዮቹም የጡረታ ፈንዱን ማዳበር፣ የአገልግሎት አሠጣጡን ማዘመንና ማሻሻል እንዲሁም የክትትልና የቁጥጥር ስራዎችን ማሳደግ ናቸው ተብሏል።
በመድረኩ ላይ የሰው ሃብት አስተዳደር፣ የስነምግባር፣ የፋይናንስ፣ ውዝፍ የመዋጮ ገቢ አሰባሰብ እና የግዢ መመሪያዎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን፣ የሪጅን ጽ/ቤቶች እና የዋናው መስሪያ ቤት የስራ ክፍሎችም ሪፖርት አቅደርበዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ እንደተገለጸው በ2016 አፈጻጸም ላይ የነበሩ ክፍተቶች በግልጽ የተለዩ መሆናቸውንና በ2017 በጀት ዓመትም በተደራጀ መልኩ ወደ ስራ መግባትና ተጠናክሮ መቀጠል ይገባል የተባለ ሲሆን፣ የተሻሻሉት አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያዎችም ሪፎርሙን በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል መልካም ዕድል መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ለተቋሙ ውጤት መሻሻል የሠራተኞች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዋሳ ከተማ በተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የተቋሙ አመራሮች፣ የሪጅንና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ኃላፊዎች እና የዋናው መስሪያ ቤት የስራ ኃላፊዎች ተካፍለዋል።