አስተዳደሩ ከአሰሪ መ/ቤቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ከመንግስት አሠሪ መ/ቤቶች ጋር ባለው የስራ ግንኙነት ዙሪያ መስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም ምክክር አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት መድረኩ በጋራ በምንሰራቸው ስራዎች ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ አገለግሎት አሠጣጥ እንዲኖር ያግዛል። አስተዳደሩ በአሰሪ መ/ቤቶች ላይ በሚያደርገው ክትትል አሁንም ድረስ የማስረጃዎች ተሟልቶ አለመምጣት የሚታይ ችግር በመሆኑ፣ በ2018 የተሻለ አፈጻጸም ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር መፍትሄ ለማምጣት ይህ አይነቱ መድረክ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት አስተዳደሩ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን የመንግስት ሠራተኞች ቆጠራ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚህ ስራ መሳካት አሠሪ መ/ቤቶች ትብብር በማድረግ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት ልትወጡ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም የብሔራዊ መለያ ቁጥር/ፋይዳ/ እንደ ሀገር ትልቅ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ አሠሪ መ/ቤቶችም የሠራተኞቻችሁን ማስረጃ ስትልኩ የፋይዳ ቁጥር መጥቀሳችሁን አረጋግጣችሁ ሊሆን ይገባል ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ አስተዳደሩም ከአሠሪ መ/ቤቶች ጋር ያለውን የመረጃ ልውውጥ የሚያቀላጥፉ ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ መተግበሪያዎችን የማልማትና የማዘመን ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ እንደተገለጸው መድረኩ ግልፅ፣ የተሟላና ወቅታዊ የማስረጃ ለውጥ አደረጃጀትና ትልልፍ እንዲኖር የማድረግ፣ ለጡረታ ባለመብቶች ቀልጧፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ግንዛቤ የመፍጠር፣ የጡረታ አበል አወሳሰን ሂደት በቀጥታ ከደመወዝ ወደ ጡረታ እንዲሆን የማድረግ እንዲሁም በተገልጋዮች ላይ የሚያጋጥሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመቅረፍ ዓላማ ያለው ነው ተብሏል።
በአስተዳደሩ ዋና መ/ቤት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከፌዴራል አሠሪ መ/ቤቶች የፋይናንስ እና የሰው ሃብት ስራ አመራር የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
://****
መስከረም 13/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ