ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን
ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን
የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘመናት በቁጭት ስሜት ውስጥ በመክተት ሌሎች ሀገራትን ሲያጠግብና ሲያበለጽግ የኖረው የአባይ ወንዝ፣ ዛሬ ቀኑ ደርሶ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገሩ ብርሃን ሊሆን በመቻሉ የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች የላቀ ደስታ የተሰማን በመሆኑ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን እንላለን።
በሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋና መነጋገሪያ የሆነና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውዝግብ ያልተለየው ሜጋ ፕሮጀክታችን ሲሆን፣ ይህን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ እነሆ ለምርቃት በቅቷል።
ግድቡ የኢትዮጵያውያንን የመስራት አቅም ያሳየ፣ የህዝቡን ቆራጥነት እና አይበገሬነት ለዓለም ያስገነዘበ፣ በብዙ ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ፣ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መድረኮችና ሚዲያዎችም ተሟጋች ዜጎችን ያገኘና ከፍተኛ የሆነ የእኔነት ስሜት የፈጠረ ሲሆን፣ የዚህን ትውልድ የአሸናፊነት ስነ ልቦና በመገንባት ለቀጣይ ድሎች በጋራ እንዲነሳ የሚያደርግ ልዩ ምልክታችንም ጭምር ነው።
ይህ የህዳሴ ግድብ እንደሀገር የተጀመሩ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን፣ መጨረስም እንደምንችል አሳይቶናል። በመሆኑም መንግስትና ሕዝብ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመተባበርና በጋራ በመቆም ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት የሚችሉ በርካታ ችግሮችን በማስወገድ ሠላም እና ልማት የሰፈነባት፣ ለኑሮ ምቹ የሆነች፣ ተወዳጅ እና ተመራጭ እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ወደ ቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር ይቻላል።
በአጠቃላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግንባታ ጅማሮ አንስቶ ፍጻሜው እስኪታወጅ ድረስ ባሉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ስራው እንዲስተጓጎል ለማድረግ በርካታ ጫናዎችን የደረሰ ሲሆን፣ ይህን ሁሉ ተቋቁመን ግድባችንን ለፍጻሜ ማድረሳችን የሁላችንም ድል፣ የሁላችንም ደስታ ነው።
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞችም ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ ከመግዛት አንስቶ ግድቡን ቦታው ድረስ ሄዶ በመጎብኘትና በፕሮጀክቱ ውስጥ የነበሩ ሰራተኞችንም አበረታተናል፤ ከጎናቸው መሆናችንንም ገልጸናል። ለወደፊቱም ከመንግስትና ከህዝብ ጎን በመሆን የአስተዳደሩን ድጋፍ በሚፈልጉ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም እንደምንሆን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።
በድጋሚም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ታላቅ ድል በማስመዝገባችሁ እንኳን ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ አለን እንላለን።
የመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር