አስተዳደሩ በይርጋለም ከተማ ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች በማስመረቅ ለአቅመ ደካማ ግለሰቦች አስረከበ

አስተዳደሩ በይርጋለም ከተማ ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች በማስመረቅ ለአቅመ ደካማ ግለሰቦች አስረከበ

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በሲዳማ ክልል በይርጋለም ከተማ ያስገነባቸውን 8 መኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ጡረተኞች ሐምሌ 7 ቀን 2016 በማስመረቅ አስረከበ።

በቤቶቹ የምረቃ መርሃግብር ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ እንዳሉት አስተዳደሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፤ ትኩረት ሰጥቶ ከለያቸው ጉዳዮች ውስጥ የጡረተኞችን ገቢ ማሻሻል ዋናው ሲሆን፣ አስተዳደሩ ከመደበኛ ስራው ባሻገርም በተለያዩ የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ያከናውናል ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር በይርጋለም ከተማ የተገነቡት 8 ቤቶች ጥራታቸውን የጠበቁና በአጭር ጊዜ የተገነቡ ናቸው። የቤቶቹን ቁልፎች ከተረከቡት ውስጥ ሰባቱ የጡረታ ባለመብቶች ሲሆኑ፣ ይህም የተቋሙ ዋና ተግባር ጡረተኞችን መደገፍ በመሆኑ የተከናወነ ነው ብለዋል። የቤቶቹ ባለዕድለኞች አቅመ ደካማ የሆኑና ለችግር የተጋለጡ በመሆናቸው የጤና ክትትል እና የዕለት ጉርስ በዘላቂነት እንዲያገኙ የይርጋለም ከተማ ነዋሪዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም አስተዳደሩ ቤቶቹን በሚያስገነባበት ወቅት የክልሉ እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ከፍተኛ ድጋፍ ያደረጉላቸው በመሆኑ ምስጋና አቅርበዋል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመው እንዳሉት፣ ክልላቸው ከአስተዳደሩ ጋር በርካታ ስራዎችን በቅርበት በማከናወን ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው የክልሉ ፋይናንስ ቢሮም የጡረታ መዋጮን በወቅቱ ገቢ በማድረግ እና ውዝፍ ክፍያን ከፍሎ በመጨረሱ አስተዳደሩ ዕውቅና ሰጥቶታል ብለዋል። እነዚህን ቤቶች በመገንባት ለአቅመ ደካማ ዜጎች በማስረከቡም አመስግነዋል።

የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሐምሌ 07/2016 ለባለዕድለኞች ያስረከባቸው ቤቶች አስፈላጊ የሆኑ የቤት ዕቃዎች የተሟሉላቸው እና ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ ዕቃ ክፍል፣ ሻወር ቤት እና መጸዳጃ ቤቶች ያሏቸው ሲሆን፣ የቤት አስቤዛም ተሟልቶላቸዋል። አስተዳደሩ የቤቶቹን የግንባታ፣ የቁሳቁስ ማሟያ እና የአስቤዛ ወጪዎችን ሙሉ በሙሉ የሸፈነ ሲሆን፣ በዕለቱም በአስቸጋሪ ኑሮ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ቤተሰቦችም ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብርም ተከናውኗል።

ቤቶቹን የተረከቡት ባለዕድለኞች በሰጡት አስተያየት ቀድሞ የሚኖሩበት ቤት ለኑሮ ምቹ ያልሆነ፣ ላለባቸው የአካል ጉዳት የማይመች፣ ዝናብ የሚያስገባ እና የተጎሳቆሉ ከመሆናቸውም በላይ ከዛሬ ነገ ወደቁብን ብለን የምንሳቀቅባቸው ነበሩ፤ አሁን ግን ቤት ያልነበረንንም ጭምር አስተዳደሩ የቤት ቁሳቁስ የተሟላባቸው ዘመናዊ ቤቶችን ስላስረከበን የአስተዳደሩን አመራሮች እና ሠራተኞች እናመሰግናለን ብለዋል።

በዕለቱ በተካሄደው የቤቶች ምረቃ እና ርክክብ መርሃ ግብር ላይ ግንባታው በአፋጣኝ እንዲከናወን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዕውቅና የመስጠት ስነ-ስርዐት የተከናወነ ሲሆን፣ በመርሃ ግብሩም ላይ የክልሉ እና የከተማው አመራሮች፣ የአስተዳደሩ አመራሮች እና የስራ ኃላፊዎች፣ የቤቶቹ ባለዕድለኞች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

Share this Post