አስተዳደሩ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደ
አስተዳደሩ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄደ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ሐምሌ 10 ቀን 2015 አከናወነ።
የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን በቀለ በችግኝ ተካላ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ ሁለተኛው ዙር መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ቆይቷል። አስተዳደሩም ከዚህ ቀደም ብሎ ሰኔ 23/2015 ጨፌ ኮንዶሚኒየም በሚባለው አካባቢ የመርሃ ግብሩ አካል የሆኑ 1500 የተለያዩ የችግኝ አይነቶችን የተከለ ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል እና ሪከርዱን የመስበር ዕቅዱን ለማሳካትም የዋናው መስሪያ ቤት እና የመሃል ሪጅን ጽ/ቤት ሠራተኞችን በማስተባበር 1000 ችግኞች እንዲተከሉ ተደርጓል። እንደ ሀገር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም የችግኝ ተከላው በሪጅን እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በኩልም ተከናውኗል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ምህዳርን ከመጠበቅ በሻገርም በምግብ ሰብል ምርት ራሳችንን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ዛሬ የምንተክለው ለመጪው ትውልድ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ሁሉም ችግኞችን በመትከል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ያሉ ሲሆን፣ አስተዳደሩም በዕቅዱ መሠረት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራዎችንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 08 ወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ድማሙ ደፋር በበኩላቸው አስተዳደሩ በወጣቶች ማዕከል የችግኝ ተከላ ማከናወኑ በተቋሙ ለሚገለገሉ ወጣቶች ምቹ እና አስደሳች አካባቢን የሚፈጥር ሲሆን፣ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ በኩልም ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ሐምሌ 10 ቀን 2015 እና በአስተዳደሩ በኩል ሰኔ 23/2015 በተከናወነው “ነገን ዛሬ እንትከል” የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በዋናው መስሪያ ቤት በኩል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 በሚገኙት ጨፌ ኮንዶሚኒየም፣ ወጣቶች ማዕከል እና ቢ 29 በሚባለው አካባቢ፣ እንዲሁም በሪጅንና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በኩል በተመረጡ የችግኝ መትከያ ቦታዎች በአጠቃላይ 16,431 የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች የተተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የአረንጓዴ አሻራ አካል በሆነው በዚህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የዋናው መስሪያ ቤት አመራሮችን ጨምሮ የሪጅን እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተካፍለዋል።