በተለያዩ የስራ ዕድሎች ለሚሳተፉ ሠራተኞች ስልጠና መስጠት ተጀመረ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በ2015 በተቋሙ ተግባራዊ ባደረገው ሪፎርም ምደባ ያላገኙ ሠራተኞች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለማሰማራት ከሰኔ 27 እስከ ሐምሌ 01 /2015 ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ መስጠት ጀመረ።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳባ ኦሪያ እንዳሉት ተቋሙ ካከናወናቸው የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች ውስጥ አንዱ የሠራተኞችን ምደባ በፍትሃዊነት ማከናወን አንዱ ሲሆን፣ በዚህም ከአጠቃላይ ሠራተኛው 85 በመቶው መስፈርቱን በማሟላታቸው በተገቢ ቦታቸው እንዲመደቡ ተደርጓል። ይህን ምደባ ለማከናወንም ከሠራተኞች ጋር አስቀድሞ ውይይት መደረጉን እና በምደባው ያልተካተቱት ሠራተኞች ደግሞ ከሁለት በላይ በመሆን በቡድን በመደራጀት ራሳቸውን መለወጥ በሚያስችላቸው የተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራት እንዲችሉ ተቋሙ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል። ባንኩም ምደባ ያላገኙ ሠራተኞችን ለተለያዩ ስራዎች የሚያዘጋጁ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ በሚኖሩበት አካባቢም ከአንድ በላይ ሆነው እንዲደራጁ ሁኔታዎችን የማመቻቸት እንዲሁም በተለያዩ መስኮች ቀድመው የተደራጁና አስተማማኝ ደረጃ ላይ የደረሱ ካሉ ከእነሱ ጋር እንዲሳተፉ በማድረግ ድርሻውን እንደሚወጣ የገለፁት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ለስራው ከሚያስፈልገው ወጪ 80 በመቶው በባንኩ፣ ቀሪው 20 በመቶው ደግሞ በሠራተኛው ይሸፈናል ብለዋል። ለዚህም ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞችን የመለየት እና ለባንኩ የማስተላለፍ ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም አስተዳደሩ ከባንኩ ጋር በመሆን የመደገፍ እና የማገዝ ኃላፊነቱን ይወጣል ያሉ ሲሆን፣ ይህ ግን በሠራተኛው ተሳትፎ ልክ የሚወሰን በመሆኑ ስልጠናውን ያለማቋረጥ በመውሰድ የተሻለ ስራ ለመስራት ዝግጁነት ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል በሚሰጠው እና ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና Business Plan Preparation and Vision Setting, Business Management and HRM, Marketing Management, Financial Statement Preparation and analysis እና Policy Environment በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል።
በዚህ ስልጠና ላይ ከዋናው መስሪያ ቤት፣ ከሪጅን እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የመጡ እና ስልጠናውን በመውሰድ በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ለመደራጀት ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞች የተካፈሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡