የጡረታ መዋጮን በተመለከተ የተደረገ ማሻሻያ
የጡረታ መዋጮን በተመለከተ የተደረገ ማሻሻያ
በአዲሱ የመንግስት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ተሻሽለው ከወጡ ድንጋጌዎች ውስጥ የጡረታ መዋጮን በተመለከተ በመንግስት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ፈንድ አስተዳደር በሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ሥር የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሂዲን ጀማል የሰጡንን ማብራሪያ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት ሥራው ከሚጠይቀው አካላዊ ብቃትና ልዩ ባህሪይ የተነሳ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ከሲቪል ሠራተኛ ባነሰ ዕድሜ ነው የሚወጡት። ከዚህ በተጨማሪ ሥራው ለአደጋ ተጋላጭ በመሆኑ አብዛኛው የጡረታ አበል ተጠቃሚ የሚሆኑት በሥራ ላይ በሚደርስ ጉዳት ነው፡፡ በዕድሜ በጡረታ የሚገለሉትም ከሲቪል መንግሥት ሠራተኛ ባነሰ ዕድሜ ሆኖ ለረዥም ዓመታት የጡረታ አበል የሚከፈላቸው ሲሆን፤ በሥራ ላይ ሆነው የሚያዋጡት የጡረታ መዋጮ ግን ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ሥራው ገብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ በጡረታ ሊሠናበቱ ይችላሉ። ነገር ግን ከተጎዱበት ጊዜ ጀምሮ በሕይወት እስካሉ እንዲሁም እነሱም ካለፉ ለተተኪዎቻቸው የጡረታ አበል ይከፈላል። ለአብነት አንድና ሁለት ዓመት የሠራ ሠው የሚያዋጣው የጡረታ መዋጮ በጣም ውስን ነው። ነገር ግን ለጡረታ የሚያበቃ ጉዳት ከደረሰበት ጡረታ ስለሚከፈለው እና የሚከፈለውም በጣም ረጅም ዓመት ስለሆነ ያዋጣው የጡረታ መዋጮ እና የሚከፈለው የጡረታ አበል በጣም ትልቅ ልዩነት ይኖረዋል።
ሌላው ከ10 ዓመት በኋላ ያለው የጡረታ አበል ስሌትም የሲቪል እያንዳንዱ ዓመት አገልግሎት በአንድ ነጥብ 25 በመቶ ነው የሚባዛው። የወታደራዊና ፖሊስ አገልግሎት የጡረታ አበል ስሌት የሚባዛው ደግሞ በአንድ ነጥብ 65 በመቶ በመሆኑ በወታደራዊና ፖሊስ ጡረታ ፈንዱ ላይ ከፍተኛ ደረጃ የወጪ ጫና ይፈጥራል፡፡
በአዋጅ 714/2003 የጡረታ መዋጮ መጠን ሲወሰን የአሠሪ ድርሻ የሲቪል አገልግሎት ከስድስት በመቶ የነበረውን ወደ 11 በመቶ እንዲያድግ በማድረግ 83 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል። በአንጻሩ የወታደራዊና የፖሊስ አገልግሎት የአሠሪ ድርሻ ከ16 በመቶ ወደ 25 በመቶ እንዲያድግ ሲደረግ፤ 56 በመቶ ብቻ ነበር ጭማሪ የተደረገው። ይህ ጭማሪ በመቶኛ ከሲቪል አገልግሎት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው፡፡ በነዚህ ምክንያቶች የወታደራዊና ፖሊስ ጡረታ ፈንድ ቀጣይነትና አስተማማኝነት ለማረጋገጥ በአዲሱ አዋጅ የአሠሪ ድርሻ መዋጮ መጠን ከ25 በመቶ ወደ 33 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል። በዚህ መሰረት ለወታደራዊና ፖሊስ አገልግሎት ጡረታ ፈንድ በመንግሥት ሠራተኛው ደመወዝ ላይ ተመስርቶ የሚደረገው መዋጮ በመንግስት መስሪያቤቱ 33 በመቶ፣ በሠራተኛው 7 በመቶ በድምሩ 40 በመቶ እንዲሆን በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል።
ሌላው ማሻሸያ የተደረገበት ነጥብ በአዋጅ ቁጥር 714/2003 ላይ ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል በመንግስት በጀት የሚተዳደሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የጡረታ መዋጮ እንደአግባቡ በገንዘብ ሚኒስቴርና በሚመለከተው የክልል አካላት እንደሚሰበሰብ ተደንግጎ ነበር፡፡ ሆኖም "በሚመለከተው የፋይናንስ አካል" የጡረታ መዋጮ ይሰበሰባል የሚለው አፈጻጸም ላይ ሲታይ ክፍተት ነበረበት። ይህም የሆነው የክልል የፋይናንስ ቢሮዎች ከምንጩ ከመሰብሰብ ይልቅ ገንዘቡን የወረዳ የፋይናስ አካላት እንዲሰበስቡ ያስተላልፋሉ። ስለዚህ ከወረዳዎች ሰብስበው ወደ ጡረታ ፈንዱ ገቢ ለማድረግ ሥራውን በጣም አዳጋች አድርጎት ቆይቷል። አፈጻጸሙም ወጥነት እንዳይኖረው አድርጓል።
በመሆኑም ድንጋጌውን ግልጽ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ የፌደራልና የክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ እንደአግባቡ በገንዘብ ሚኒስቴርና በክልሎች የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት/ ፋይናንስ/ ቢሮ ተሰብስቦ በአዋጁ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ እንዲያደርጉ ተደንግጓል። ስለዚህ ከዚህ በኋላ የክልል የፋይናንስ ቢሮዎች የጡረታ መዋጮውን ወደ ወረዳዎች የሚበትኑበት ምንም አይነት ህጋዊ ድንጋጌም ሆነ አግባብ አይኖርም ማለት ነው።
ተቋሙ ከተሰጠው ዋና ዋና ሥልጣን መካከል የጡረታ መዋጮ በአግባቡ ተሰብስቦ በወቅቱ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ ስለመደረጉ የመቆጣጠር፣ የመመርመርና የማጣራት ሥራ በውክልና የጡረታ መዋጮ በሚሰበስቡት አካላት እና የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ላይ በመገኘት እንደሚያከናውን የሚታወቅ ነው፡፡ በመሆኑም በውክልና የጡረታ መዋጮ በሚሰበስቡና አሠሪ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የጡረታ መዋጮውን ሰብስበው ገቢ ስለማድረጋቸው ለመመርመርና ለመቆጣጠር የሚያስችል ግልጽ የሆነ ድንጋጌ ባለመኖሩ አስተዳደሩ የጡረታ መዋጮ ሰብሳቢ አካላትን እና አሰሪ መሥሪያ ቤቶችን በመከታተል፣ በመመርመር እና በማጣራት በወቅቱ የጡረታ መዋጮ ሰብስበው ገቢ በማያደርጉት ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስልጣን እንዲኖረው ግልጽ ድንጋጌ ማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ስለዚህ አዲስ በተሻሻለው አዋጅ የሚሰበሰበውን የጡረታ መዋጮ በትክክልና በወቅቱ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ ስለመደረጉ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ የክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት /ፋይናንስ/ ቢሮዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ በውክልና የጡረታ መዋጮ በሚሰበስቡ አካላት እና አሰሪ መሥሪያ ቤቶች በመገኘት የመቆጣጠርና ምርመራ (ኦዲት) በማድረግ የማጣራት እንዲሁም በተገቢው ጊዜ ገቢ በማያደርጉት ላይ ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ይኖረዋል። ህጋዊ እርምጃ የሚያስወስድ ድንጋጌ ሲቀመጥ ደግሞ አፈጻጸም ላይ ትልቅ ለውጥ ይፈጥራል ሲሉ የህግ ባለሙያው አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 22/2014