አስተዳደሩ በመተግበሪያ ሶፍትዌር ልማት ላይ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር ምክክር አካሄደ
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የተቋሙ የአይ.ቲ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የመተግበሪያ ሶፍትዌር ማልማት፣ የዳታ ሴንተር እና ሌሎች ስራዎችም ላይ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር ነሐሴ 03 ቀን 2014 በዋናው መስሪያ ቤት ምክክር ተካሄደ፡፡
በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው አስተዳደሩ የሚያከናውናቸውን ተግባሮች በጥልቀት በማጥናት እና ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችም ጋር በቅርበት በመስራት መተግበሪያውን ዕውን ለማድረግ እንደሚሰሩ ከዩኒቨርስቲው የመጡ ተወካዮች የገለጹ ሲሆን፣ ስራውን ስለሚያከናውኑበት መንገድ የሚያስረዳ ፕሮፖዛልም አቅርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
አስተዳደሩ የሚሰጠውን አገልግሎት በማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ላለፉት አራት ዓመታት የአይ.ቲ ፕሮጀክት ቀርፆ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቱም የኔትዎርክ ዝርጋታ፣ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የመንግስት ሠራተኞችንና ከ700 ሺህ በላይ ጡረተኞችን ፋይል ወደ ዲጂታል ቅርጽ መቀየር እንዲሁም መተግበሪያ(Application) ማልማትን ያካተተ ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የኔትዎርክ ዝርጋታው የኤጀንሲውን አሥር ሪጅን ጽ/ቤቶች ከዋናው መ/ቤት ጋር ዘመናዊ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የዲጂታይዜሽን ስራውም የተጠናቀቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዕለቱ የተካሄደው ምክክርም አስተዳደሩ ስራዎቹን ለማዘመን ትኩረት ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የመተግበሪያ ልማቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅም የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡