- ቀን: Dec 29 2023
- አባሪ: ማውረድ
-
ይዘት
የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር
ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ያልከፈለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሀብት ስለመያዝና ስለመሸጥ
የወጣ ረቂቅ መመሪያ ቁጥር -----/2016
ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩን የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሀብት ስለመያዝና ስለመሸጥ የወጣ
መመሪያ ቁጥር --------/2016
በአዋጅ ቁጥር አንቀጽ 1267/2014 አንቀፅ 12 ንዑስ አንቀጽ 12 እና አንቀፅ 61 (2) በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ይህንን መመሪያ አውጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
- አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ያልከፈለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሀብት ስለመያዝና ስለመሸጥ የወጣ መመሪያ ቁጥር------/2016 ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
- ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር ለዚህ መመሪያ አፈፃፀም፡-
1) ‹‹ ሀብት›› ማለት የመያዣ ትዕዛዝ ሊወጣባቸው ከማይችሉት ሀብቶች በስተቀር ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ በሊዝ የያዘውን መሬት ጨምሮ ማናቸውም ቤት ወይም ህንጻ፣ ሥራ የሚከናወንበት ድርጅት፣ የማይንቀሳቀስ ፣ ልዩ ተንቀሳቃሽ ፣ልዩ ልዩ እቃዎች፣ ቼኮች የሚተላለፉ ሰነዶች፣ ቦንዶች ወይም ለገንዘብ የተሰጡ ሌሎች ዋስትናዎች፣ በኩባንያ ውስጥ ያለው የአክሲዮን ድርሻ፣ በጋራ በተያዙ ሀብቶች ላይ ያለው ድርሻ ወይም ማናቸውም ሊሸጡ የሚችሉ ሌሎች ሀብቶች ናቸው፡፡
2) ‹ሀብት ማስከበር›› ማለት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩን ሀብት ወይም ንብረት ከመያዙ በፊት ባለበት እንዲቆይና እንዳይንቀሳቀስ የሚወስደው እርምጃ ነው፡፡
3) ‹‹ውዝፍ የጡረታ መዋጮ›› ማለት በወቅቱ ያልተከፈለ የጡረታ መዋጮን፣ ወለድንና ቅጣትን ይጨምራል፡፡
4) ‹‹መያዝ›› ማለት በማናቸውም መንገድ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋይ መስሪያ ቤቱን ሀብት መያዝ እንዲሁም የጡረታ ከፋዩ መስሪያ ቤት የሆነ ገንዘብ/ሀብት በእጁ ከሚገኝ ሰው ላይ የጡረታ መዋጮ መሰብሰብን ይጨምራል፡፡
5) ‹‹ አስተዳደር ›› ማለት በደንብ ቁጥር 522/2015 የተቋቋመው የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ነው፡፡
6) ‹‹ አዋጅ›› ማለት የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1267/2014 ነው፡፡
7) ‹‹ደንብ›› ማለት የመንግስት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 522/2015 ነው፡፡
8) ‹‹ሠው ›› ማለት የተፈጥሮ ሠው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው
- ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ አስባሰብ ተግባር ሀብት የሚሰበሰብበት መንገድ
- አስተዳደሩ የጡረታ መዋጮ በወቅቱ ያልከፈለ አሰሪ መስሪያ ቤት አካውንቱ ላይ በቂ ገንዘብ አለመኖሩ ከተረጋገጠ የሚፈለግበትን የጡረታ መዋጮ በሚከተለው አኳኋን ሊሰበሰብ ይችላል፡፡
ሀ) ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለ ዕዳውን የሚንቀሳቀስ ሀብት በመያዝ እና በመሸጥ፣
ለ) ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለ ዕዳውን የማይንቀሳቀስ ወይም ልዩ ተንቀሳቃሽ ሀብት በማስከበር፣ በመያዝ እና በመሸጥ፣
ሐ) ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ግዴታውን ያልተወጣ መስሪያ ቤት በእጁ የሚገኝውን ሀብት ለአስተዳደሩ እንዲያስረክብ ወይም በአዋጁ የተጣለበትን ግዴታ እንዲወጣ በማድረግ
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለ ዕዳው ሥራውን የሚያከናውንባቸውን ማንኛውንም ንብረት ጨምሮ ማናቸውም የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ሀብት እስኪሸጥ ድረስ የማስተዳደር ተግባር የሚከናወነው አስተዳደሩ በሚመድባቸው ተረካቢዎች ይሆናል፡፡
- የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሥልጣንና ተግባር
የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ፤-
- የውዝፍ የጡረታ መዋጮ ውሳኔ ማስታወቂያ ደርሷቸው የሚፈለግባቸውን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ላልከፈለ ከዚህ መመሪያ ጋር በተያያዘ አባሪ መሰረት የክፍያ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ያልከፈለ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ አሰባሰቡን የሚያደናቅፍ ሀብት የማሸሽ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ተግባር በመፈጸም ላይ ያለ መሆኑን ሲረዳ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳ ክፍያ ማስታወቂያ ከተላከ በኋላ መቆየት ያለበትን የ30 ቀናት ጊዜ ገደብ ሳይጠብቅ በአፋጣኝ ሀብቱን የመያዝ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡
- የሚያዝው ሀብት የሚበላሽ ዕቃ በሚሆንበት ጊዜ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳ ክፍያ ማስታወቂያ ከተላከ በኋላ መቆየት ያለበትን የ30 ቀናት ጊዜ ገደብ ሳይጠብቅ ዕቃው የሚሸጥበትን ጊዜና ስርዓት ይወስናል፡፡
- ሀብት ስለመያዝ የሚሰጥ ማስታወቂያ የደረሰው ወይም ሀብቱ የተያዘበት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋይ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳውን የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምለት ወይም በየጊዜው በሚደረግ ክፍያ የሚፈለግበትን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ለመፈጸም እንዲፈቀድለት በሚያቀርበው ጥያቄ ላይ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
- በውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳ ምክንያት የተያዘ ሀብት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በግልጽ ጨረታ የሚሸጥበትን ዘዴ ሊወስን ይችላል፡፡
- በውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳ ምክንያት የተያዘን ሀብት ለመሸጥ የሚሰራጨውን የግልጽ ጨረታ ሽያጭ ሰነድ ያጸድቃል፡፡
- በዚህ መመሪያ መሰረት ከሁለተኛ ጊዜ ግልጽ ጨረታ በኋላ ያልተሸጠን ሀብት በመነሻ ግምቱ ዋጋ ለአስተዳደሩ እንዲዛወር ያደርጋል፡፡
- በቂ ምክንያት ሲኖረው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳውን ሀብት የመያዝና የመሸጥ አፈጻጸም እንዲቆም ያደረጋል፡፡
- በውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳ የተያዘን ሀብት የመያዝና የመሸጥ ተግባር በሶስተኛ ወገን እንዲከናወን ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡
ክፍል ሁለት
ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩን ሀብት ስለመያዝ
- ሀብትን ስለመያዝ የሚሰጥ ማስታወቂያ፡-
ሀብትን ስለመያዝ የሚሰጥ ማስታወቂያ የሀብት መያዝ እርምጃ ከመወሰዱ ከ30 ቀናት አስቀድሞ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ መስጠት ወይም መድረስ ያለበት ሲሆን ማስታወቂያውም ከዚህ መመሪያ ጋር በተያያዘው አባሪ 3 የተዘረዘሩትን የሚከተሉትን መረጃዎች የያዘ መሆን አለበት፡፡
- ከአስተዳደሩ ቀደም ሲል ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ የተላከውን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ውሳኔ ማስታወቂያ ቀን፤
- ከውዝፍ የጡረታ መዋጮ የሚፈለገውን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ የገንዘብ መጠን፤
ሀ. የሚጠበቅበትን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ፤
ለ. በመንግሥት የልማት ድርጅትና በራሱ ገቢ የሚተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ ማስታወቂያው እስከተላከበት ጊዜ ድረስ የታሰበው ወለድ፤
ሐ. በመንግሥት የልማት ድርጅትና በራሱ ገቢ የሚተዳደር የመንግሥት መሥሪያ ቤት ላይ መቀጮ፤
መ. አስቀድሞ የተከፈለ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ ተቀናሽ የተደረገ መሆኑን፣ እና
ሠ. በቀሪነት የሚፈለግበትን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ
- አስተዳደሩ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩን ሀብት በመሸጥ ከሽያጭ የሚገኘውን ገንዘብ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳውን ብቻ ሳይሆን ሀብቱን ከመሸጥ ጋር በቀጥታ ለተያያዙ የአፈጻጸም ተግባሮች ማከናወኛ ለሚወጣ ወጪ መሸፈኛ የሚያውለው መሆኑን በማስታወቂያው ውስጥ መግለፅ ይኖርበታል፡፡
- ሀብትን ስለመያዝ ማስታወቂያ ስለሚሰጥበት መንገድ
- ሀብትን ስለመያዝ የሚሰጠው ማስታወቂያ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ በሚከተለው አኳኋን እንዲደርስ ይደረጋል፡፡
ሀ) ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ አሠሪ መሥሪያ ቤት መዝገብ ቤት ገቢ በማድረግ
ለ) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1ሀ) መሠረት የሚሠጥ ማስታወቂያ ማስታወቂያውን የሚቀበለው ወይም የሚረከበው ሰው በማስታወቂያው ቅጅ ላይ የተቀበለ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲሆን የተቋሙን ማህተም በማድረግ ስሙንና የተረከበበትን ቀን በመጻፍ ሊፈርም ይገባል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1ለ) መሰረት ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ማስታወቂያውን መስጠት ካልተቻለ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ መሥሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ወይም በር ላይ አመችና በግልጽ በሚታይ ስፍራ ሶስት እማኞችን በማስፈረም ወይም የፖሊስ መኮንን በተገኘበት እንዲለጠፍ ይደረጋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1ና2 መሰረት ማስታወቂያውን ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ማድረስ ካልተቻለ እንደ አስፈላጊነቱ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ኢሜልና ፋክስን ጨምሮ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ በማስተላለፍ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ የተመለከቱትን ዘዴዎች በመጠቀም ማስታወቂያ ማድረስ ካልተቻለ የፍርድ ቤት ማስታወቂያ በሚወጡበት ጋዜጣ ማስታወቂያውን በማውጣት ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋይ መስሪያ ቤት እንዲደርስ ይደረጋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት የፍርድ ቤት ማስታወቂያ በሚወጣበት ጋዜጣ የሀብት መያዣ ትዕዛዝ የወጣበት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ውሳኔ ማስታወቂያ እንደደረሰው ይቆጠራል፡፡
- ሀብት ከመያዙ በፊት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች
- አስተዳደሩ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ውሳኔ ማስታወቂያ ካደረሰበት ወይም ውዝፍ የጡረታ መዋጮው በምርመራ ከተገኘበት ወይም በዚህ መመሪያ አንቀጽ 6 መሠረት ማስጠንቀቂያ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለ ዕዳውን ሀብትና የሥራ እንቅስቃሴ የሚመለከት መረጃ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን ማሰባሰብ አለበት፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የሚሰበሰበው መረጃ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለ ዕዳውን ሀብት ዓይነት፣ ብዛት፣ የሚገኝበትን አድራሻ፣ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ሀብት በማን ይዞታ ሥር እንደሚገኝ፣ በዋስትና የተመዘገበ መሆን አለመሆኑን እና የመሳሰሉ መረጃዎችን የሚጨምር መሆን አለበት፡፡
- በተሰበሰበው መረጃ ወይም በተገኘ ጥቆማ መሰረት የአስተዳደሩ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ አሰባሰብ የሚያደናቅፍ ሁኔታ መኖሩን የተረዳ እንደሆነ እና ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆኑ ከታወቀ በ30 ቀናት የጊዜ ገደብ ወይም በማስጠንቀቂያ የተሰጠውን ቀነ ገደብ ሳይጠብቅ አስተዳደሩ ሀብቱን በመያዝ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ የመሰብሰቡ አፈፃፀም እንዲካሄድ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለ ዕዳው ሀብት በእጁ በይዞታው የሚገኝ ማንኛውም ሰው፣ ሀብቱን ወይም መብቱን ለሚመዘግብ አግባብ ላለው ለአስተዳደሩ ሠራተኛ መስጠት አለበት፡፡
- ሀብትን ስለ ማስከበር
- አስተዳደሩ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ማስጠንቀቂያውን ለመላክ ሲወስን ወዲያውኑ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ሀብት በዋስትናነት እንደተሰጠ ሀብት ሳይሽጥ፣ ሳይለወጥ ሳይከፈል፣ በባለሀብትነትም ሆነ በይዞታ ሳይዛወር ተከብሮ እንዲቆይ እንዲያደርግ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ፣ ሀብት ለሚመዘግብ አግባብ ያለው የመንግስት አካል ወይም የግል ድርጅት ወይም ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ሀብት በእጁ ለሚገኝ ሰው ማስታወቂያ ይልካል፡፡
- ሀብት ተከብሮ እንዲቆይ የሚሰጥ የማስታወቂያ ይዘት ከዚህ መመሪያ ጋር በተያያዘው አባሪ 1 እና 2 የተዘረዘሩትን መረጃዎች የያዘ መሆን አለበት፡፡
- ሀብት የሚመዘግበው አካል በውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ስም የተመዘገበ ሀብት ተከብሮ እንዲቆይ ማድረግና የተከበረውን ሀብት ዓይነት ለአስተዳደሩ ማስታወቅ አለበት፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ሀብት በእጁ የሚገኝ ማናቸውም አካል ሀብት የማስከበሩ ማስታወቂያ ባይደርሰው ኖሮ ሀብቱን ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ የሚያስረክብ መሆኑን እና ሀብቱ በእጁ ወይም በይዞታው እንዲቆይ መደረጉ ወጪ ያስከተለበት መሆኑን በበቂ ማስረጃ አስደግፎ ያቀረበ እንደሆነ የዚህ ዓይነቱ ወጪ ተስልቶ ከሀብቱ ሽያጭ ከተገኘ ገቢ ላይ እንዲከፈለው ይደረጋል፡፡
- ስለ ማይከበሩና ስለ ማይያዙ ሀብቶች
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ መስሪያ ቤት በግብርና ስራ የሚተዳደር ከሆነ በአስተዳደሩ አስተያየት ለስራው አገልግሎት በቂ ሆነው የሚገመቱ የቀንድ ከብቶች፣ የጋማ ከብቶች፣የዘር እህልና ፍጹም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች፣
- እንደ መንግሥት መስሪያ ቤቱ አግባብ ለተቋቋመበት አላማ ለማስፈፀም ለሥራቸው አግባብነት ያላቸውን እና ለጠቅላላው ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ንብረቶች፣
- እንዳይከበር፣ እንዳይሸጥና ለዕዳ መክፍያ እንዳይሆን በማናቸውም ሌላ ሕግ ወይም በፍርድ ቤት የተወሰነ ማናቸውም ዓይነት ሀብት፣
- ለዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀፅ 1 አፈጻጸም አስተዳደሩ የማይከበር ሀብትን መጠን ሊወስን ይችላል፡፡
- ሀብት ስለመያዝ
- በዚህ መመሪያ አንቀጽ 6 መሠረት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋይ ማስጠንቀቂያው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳውን ያልከፈለ እንደሆነ ወይም በአስተዳደሩ ቀርቦ የመክፈያ ጊዜ እንዲሰጠው ያላደረገ ወይም በቂ ዋስትና ያላቀረበ እንደሆነ በዚህ መመሪያ በአንቀጽ 9 ከመያዝ ነጻ ከተደረጉት ወይም በፍ/ቤት አስቀድሞ ከተከበረ ወይም በዋስትና ከተያዘ ሀብት በስተቀር ማናቸውንም ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳውን ሀብት አስተዳደሩ ይይዛል፣ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳው ክፍያ እንዲወል ያደረጋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገው ቢኖርም አስተዳደሩ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ክፍያ አሰባሰቡን የሚያደናቅፍ፣ ሀብት የሚያሸሽ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ተግባር በመፈጸም ላይ ያለ መሆኑን ሲረዳ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ክፍያ ማስታወቂያ ከተላከ በኋላ መቆየት ያለበትን የ30 ቀናት ጊዜ ገደብ ሳይጠብቅ በአፋጣኝ ሀብቱን የመያዝ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የሚያዘው ሀብት በተቻለ መጠን ከውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ከሚፈለገው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ እዳ ጋር ተመጣጠኝ መሆን አለበት፡፡
- አስተዳደሩ ሀብት ከመያዙ በፊት ሀብቱ እንዲያዝ የተሰጠውን የውሳኔ/የትዕዛዝ ቅጅ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 6 ለተገለጹት አካላት መሰጠት አለበት፡፡
- ከእርሻ ሰብል በስተቀር
ሀ) ማናቸውም የሚንቀሳቀስ ሀብት የሚያዘው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው እጅ የሚገኘውን ሀብት በመረከብ ነው፡፡
ለ) ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው መስሪያ ቤት ሀላፊ ወይም ወኪል በተገኘበት አስተዳደሩ ሀብቱን ቆጥሮና መዝግቦ ይረከባል፣ በቦታው የተገኙት ሁሉ የተቆጠረውን ሀብት በፊርማቸው ያረጋግጣሉ፣ የተቆጠረው ሀብት ዝርዝር ቅጅ ለውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ይሰጣል፡፡ ለመቅረብ ፈቃደኛ ካልሆነ በሌለበት ይቆጠራል ፡፡
ሐ) የተያዘው ሀብት የከበሩ ማዕድናት ማለትም አልማዝ፣ እንቁ፣ወርቅና ብር ወ.ዘ.ተ የሆነ እንደሆነ መጠኑ በሚዛን ተመዝኖ እና የጥራት ደረጃው ተመርምሮ ዋጋው በባለሙያ ተገምቶ በዝርዝሩ ላይ መገለጽ አለበት፡፡
- የተያዘው ወይም የተከበረው ሀብት በቀላሉ የሚበላሽ ወይም ዋጋ የሚያጣ /የሚቀንስ የሆነ እንደሆነ አስተዳደሩ በማናቸውም ዘዴ ወዲያውኑ ሊሸጠው ይችላል፡፡
- የሚያዘው ወይም የሚከበረው ሀብት የእርሻ ሰብል ወይም ፍራፍሬ የሆነ እና በማሳው ላይ ያለ ከሆነ ትዕዛዙን በሥፍራው በመለጠፍ፣ ሰብሉ ታጭዶ የተከመረ ወይም በመወቃት ላይ ያለ ወይም የእንሰሳት መኖ ክምር ከሆነ በክምሩ ወይም በአውድማው አቅራቢያ በመለጠፍ ይሆናል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 7 የተከበረው ሀብት ስለሚጠበቅበት ሁኔታ አስተዳደሩ የሚሰጠው ትዕዛ እንደተጠበቀ ሆኖ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ሰብሉን የአስተዳደሩ ተወካይ ባለበት ሊያጭድ ወይም ሊወቃ ይችላል፡፡
- ለዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 8 አፈጻጸም ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ሰብሉን ካጨደ ወይም ከወቃ በኋላ የተገኘውን የምርት መጠን የአስተዳደሩ ወኪል ባለበት ተቆጥሮ ሁሉም እንዲፈራረሙ ከተደረገ በኋላ ሃብቱ የሚጠበቅበትንና የሚሸጥበትን ሁኔታ አስተዳደሩ ይወሰናል፡፡
- እንዲያዝ ወይም እንዲከበር የታዘዘው ሀብት በውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው እጅ ያልገባ ከሌላ ሰው የሚጠይቀው በሚተላለፍ ሰነድ ያልተደገፈ ገንዘብ ወይም በፍርድ ቤት ክስ በማስፈረድ መብት ያገኘበት ገንዘብ ወይም ሌላ ሀብት በሆነ ጊዜ አስተዳደሩ ሌላ ግልጽ የሆነ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ሀብቱ ወይም ገንዘቡ በእጁ ያለ ሰው ገንዘቡን ወይም ሀብቱን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳውም ሆነ ለሌላ ማናቸውም ሰው ሳይሰጥ /ሳያስተላልፍ በእጁ እንዲቆይ በጽሁፍ ማዘዝ ይኖርበታል፡፡
- የሚያዘው ወይም የሚከበረው ሀብት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ከሌሎች ሰዎች ጋር በተካፋይነት ወይም በጋራ የሚጠቀምበት ወይም የጋራ ባለሀብት የሆነበት ሀብት ወይም በሽርክና የያዘው ሀብት ወይም በውርስ የተገኘ ሀብት ሲሆን የመያዙ ወይም የማስከበሩ ሥርዓት የሚፈጸመው ድርሻውን ለሌላ ሰው አሳልፎ እንዳይሰጥ፣እንዳይሸጥ፣ በዋስትና እንዳያሲዝ ወይም በማናቸውም ምክንያት እንዳያስተላልፍ ከሽርክናው የሚያገኘውን ትርፍ እንዳይወስድ የማገድ ትዕዛዝ ለጋራ ባለሀብቶቹ ወይም ለሸሪኮች በመስጠት ነው፡፡
- እንዲያዝ የታዘዘው ሀብት የሚተላለፍ የገንዘብ ሰነድ የሆነ እንደሆነ እና በፍርድ ቤት ወይም በመንግስት መስሪያ ቤት ያልተያዘ ከሆነ የማስከበሩ ወይም የማስያዙ ሥርዓት የሚፈጸመው የሚተላለፈው የገንዘብ ሰነድ ተይዞ በአስተዳደሩ እንዲቀመጥ በማድረግ ወይም በሌላ አካል የተያዘም ከሆነ ሌላ ትእዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ እንዳይለቀቅ የሚያግድ ትእዛዝ በመስጠት ይሆናል፡፡
- እንዲያዝ ወይም እንዲከበር የታዘዘው ሀብት በፍርድ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ወይም በመንግስት መስሪያ ቤት እጅ የሚገኝ ከሆነ ሀብቱ ወይም ሀብቱ የሚያስገኘው ማናቸውም ጥቅም ተጠብቆ እንዲቆይ አስተዳደሩ ትዕዛዝ በመስጠት ማስከበር ይችላል፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው በውድ እቃዎች ማስቀመጫ ሳጥን ውስጥ ስላለው ሀብት መረጃ እንዲሰጥ ተጠይቆ ፈቃደኛ ካልሆነ ወይም ቁልፉን ለመስጠት እምቢተኛ ከሆነ ባንኩ ወይም የገንዘብ ተቋሙ ቁልፉን እንዲሰጥ በማድረግ የባንኩ ተወካይና ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳ ወይም ወኪሉ እንዲገኙ ማስታወቂያ በመስጠት በአስተዳደሩ ተከፍቶ ሀብቱ እንዲመዘገብና እንዲታሸግ ይደረጋል፡፡
- የመንግስት ቦንድ ወይም ከኢንቨስትመንት ወይም ከኢንሹራንስ በየጊዜው የሚከፈል ሂሳብ እንዳይከፈልና ሌላ ትዕዛዝ በአስተዳደሩ እስከሚሰጥ ድረስ ተይዞ እንዲቆይ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ በመስጠት ሊከበር ይችላል፡፡
- እንዲያዝ ወይም እንዲከበር የተወሰነው የማይንቀሳቀስ ወይም ልዩ ተንቀሳቃሽ ሀብት ከሆነ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ሀብቱን ለሌላ ሰው እንዳይሰጥ፣ እንዳይሸጥ፣ እንዳይለውጥ ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ መብቱን ለማንም ሰው እንዳያዛውር እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በሀብቱ ላይ የዋስትና መብትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት መብት እንዳይኖራቸው የሚያግድ ትዕዛዝ የማይንቀሳቀስ ሀብት ለሚመዘግበው አካል በመስጠት የሚፈጸም ይሆናል፡፡
- ልዩ ጥንቃቄ ስለሚያስፈልጋቸው እቃዎች
- በዚህ መመሪያ አንቀጽ 1 በተመለከተው መሠረት ሀብት ሲያዝ ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ልዩ ልዩ ኬሚካሎች ወይም ንጥረ ነገሮች የሚሸጡባቸው፣ የሚከማቹባቸው ወይም የሚመረቱባቸው ሲሆን እነዚህን ኬሚካሎች ወይም ንጥረ ነገሮች ለመያዝ የሚያስፈልገው ጥንቃቄ በቅድሚያ መታወቅና አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል፡፡
- አስተዳደሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ሀብት ከመያዙ በፊት ወይም/እና በኋላ ሊበላሽ የሚችልበት ሁኔታ ካለ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ዝርዝር ሥርዓት ሊያወጣ ይችላል፡፡
- አስተዳደሩ በዚህ አንቀጽ በተመለከተው መሰረት ልዩ ጥንቃቄ የሚሹ እቃዎች ስለአያያዙ፣ ስለአጠቃቀሙና አሻሻጡ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ትብብር ሊጠይቅ ይችላል፡፡
- የተያዘ ወይም የተከበረ ሀብት ስለሚለቀቅበት ሁኔታ
- የተያዘ ወይም የተከበረ ሀብት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው የተያዘው ወይም የተከበረው ሀብት በሙሉ የተከፈለ ወይም ለመክፈል ዋስትና ያስያዘ መሆኑን በመግለፅ የሀብቱ ሽያጭ ከመካሄዱ በፊት ለአስተዳደሩ አቤቱታ ሲያቀርብለት አቤቱታውን በማጣራት ውሳኔ ይሰጣል፡፡
ሀ) ለሀብቱ መያዝ ወይም መከበር ምክንያት የሆነው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ እንዲሁም ንብረቱን ለማስያዝና ለማስከበር የተደረጉት ወጭ በሙሉ የተከፈለ እንደሆነ፣
ለ) ለሀብቱ መያዝ ወይም መከበር ምክንያት የሆነው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ ዋስትና በማስያዝ በስምምነት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ መክፈያ ጊዜው የተራዘመ እንደሆነ፣
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ሀብት የተለቀቀ በሚሆንበት ጊዜ አስተዳደሩ በውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው ወጪ ሀብቱን ለሚመዘግብ አካል የመያዝ ወይም የማስከበሩ ትዕዛዝ መነሳቱን መግለጽ አለበት፡፡
- በተያዘ ወይም በተከበረ ሀብት ላይ የሚቀርብ አቤቱታን ስለመመርመር
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው የተያዘው ወይም የተከበረው ሀብት በሕግ የማይከበር ወይም የማይያዝ ነው በማለት የሀብቱ ሽያጭ ከመካሄዱ በፊት ለአስተዳደሩ አቤቱታ ሲያቀርብለት አቤቱታውን በማጣራት ውሳኔ ይሰጣል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ውሳኔው ሀብቱ መያዝ የለበትም የሚል ከሆነ ሀብቱ እንዲለቀቅ ይደረጋል፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው ዕዳውን ባለመክፈሉ ምክንያት አስተዳደሩ የያዘው ወይም ያስከበረው ሀብት ይገባኛል የሚሉ ሦስተኛ ወገኖች የሚያቀርቡትን አቤቱታ አስተዳደሩ ተቀብሎ ይመረምራል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ሀብቱ አላግባብ የተያዘ መሆኑን እና የአቤቱታ አቅራቢው ሀብት መሆኑን በበቂ ማስረጃ ያረጋገጠ እንደሆነ አስተዳደሩ የተያዘውን ሀብት እንዲለቀቅ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
- ሀብትን በመያዝ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ መክፈያ ማዋልን በውክልና ስለማስፈፀም
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው ሀብት የሚገኘው ከአስተዳደሩ ዋና መ/ቤት ወይም ሪጂን ጽ/ቤት አካባቢ ርቆ በሚገኝ ቦታ እንደሆነ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳው ሀብት እንዲያዝ የተሰጠውን ውሳኔ ከአስፈላጊ ሰነዶች ጋር በመላክ ሀብቱ በሚገኝበት አካባቢ ባለው የአስተዳደሩ ፅ/ቤት አማካይነት በውክልና እንዲፈፀም ሊያደርግ ይችላል፡፡
- ሀብቱ እንዲያዝ የተሰጠው ውሳኔና አስፈላጊ ሠነዶች የደረሰው የአስተዳደሩ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀብቱን በመያዝ በመሸጥ ገንዘቡን ለወከለው አካል ማስተላለፍ አለበት፡፡
ክፍል 3
የተያዘውን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳውን ሀብት ስለመሸጥ
- ሀብትን ስለመገመት
- አስተዳደሩ ያስከበረው፣ የያዘው ወይም ታሽጎ እንዲቀመጥ ያደረገውን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩን ሀብት ለመሸጥ እንዲችል የሀብት ግምት ሥራ ማከናወን በሚችሉ በሚመለከታቸው ሶስተኛ ወገን እንዲገመት ያደርጋል፡፡
- በዚህ ዓይነት የተገመተው የሀብት ዋጋ የግልጽ ጨረታ መነሻ ዋጋ ሆኖ ይወሰዳል፡፡
- ሀብት ስለሚሸጥበት ዘዴ
- አስተዳደሩ የተያዘውን ወይም የተከበረውን ሀብት ዓይነት፣ ያለበትን ቦታ፣የሀብቱ ሁኔታ እና ሌሎች ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሽያጩ በግልጽ ጨረታ ዘዴ የሚከናወን መሆኑን ይወስናል፡፡
- የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በአስተዳደሩ የተያዘው ወይም የተከበረው ሀብት የሚበላሽ ዕቃ በሚሆንበት ጊዜ የግልጽ ጨረታ ሂደቱን ሳይከተል ሀብቱ የሚሸጥበትን ሌላ ዘዴ አስተዳደሩ ይወስናል፡፡
- አስተዳደሩ በግልጽ ጨረታ የሚሸጠው ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ሀብት ከአንድ በላይ ከሆነ እንደሁኔታው ሀብቱ በሙሉ በአንድ ጊዜ ወይም ከፊል ሀብቶቹ በቅደም ተከተል እንዲሸጡ ለማድረግ ይችላል፡፡
- የሀብት ሽያጭ በቅደም ተከተል የሚደረገው የከፊል ሀብቱ ሽያጭ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳውን ለመሸፈን የሚበቃ መሆኑ እና ሀብቱን ለመሸጥ ብዙ ጊዜ የማይወስድ መሆኑ ሲታመን ነው፡፡
- የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ስለማውጣት
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ ምክንያት የተያዘው ሀብት በግልጽ ጨረታ የሚሸጠው የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ሰፊ ሥርጭት ባለው ጋዜጣ ላይ እንዲወጣ በማድረግ ነው፡፡
- የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያው የሀብቱ ዓይነት፣የሀብቱ የግልጽ ጨረታ መነሻ ግምት፣ ሀብቱ የሚገኝበትን ቦታ፣ግልጽ ጨረታው የሚካሄድበትን ቀንና ሰዓት፣የሀብቱን ባለቤት ስም፣ በግልጽ ጨረታው ተሳታፊዎች በጨረታው ለመካፈል የጨረታ ማስከበሪያ በባንክ በተመሰከረለት ቼክ ወይም በሲፒኦ ወይም በጥሬ ገንዘብ እንዲያስይዙ እና አስተዳደሩ ግልጽ ጨረታውን የመሰረዝ መብት እንዳለው የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡
- የግልጽ ጨረታው ማስታወቂያ ከዚህ መመሪያ ጋር አባሪ በተደረገው ፎርም ዓይነት መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡
- ማናቸውም የሚንቀሳቀስ ሀብት ሽያጭ በግልፅ ጨረታ የሚከናወነው የግልፅ ጨረታው ማስታወቂያ ጋዜጣ ላይ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ቢያንስ አስራ አምስት የስራ ቀናት በኋላ መሆን አለበት፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሚሸጠው የማይንቀሳቀስ ወይም ልዩ ተንቀሳቃሻ ሀብት የሆነ እንደሆነ ሽያጩ የሚከናወነው የግልጽ ጨረታው ማስታወቂያ ጋዜጣ ላይ ከወጣበት ቀን አንስቶ ከ30 የስራ ቀናት በኋላ ይሆናል፡፡
- የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ በጋዜጣ ከወጣ በኋላ የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ያለበትን ገፅ ፎቶ ኮፒ በማድረግ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በመለጠፍ በግልጽ ጨረታው የሚካፈሉት ሰዎች ብዛት እንዲጨምር ጥረት መደረግ አለበት፡፡
- በግልጽ ጨረታ የሚሸጠው ሀብት ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ከሆነ በግልጽ ጨረታው የሚሸጠውን ሀብት በሬዲዮ ወይም በምስል በማስደገፍ ማስታወቂያ በቴሌቪዥን እና በዌብሳይት እንዲተላለፍ ሊደረግ ይችላል፡፡
- ግልጽ ጨረታ ስለማካሄድ
- የግልጽ ጨረታ ሥነ-ሥርዓቱ ከመጀመሩ በፊት በግልጽ ጨረታ ሰነድ የገዙ ሰዎች ስም ዝርዝር ይመዘገባል፣ በግልጽ ጨረታው ተሳታፊዎች በጨረታው ለመካፈል ተገቢውን መያዣ በባንክ በተመሰከረለት ቼክ ወይም በሲፒኦ ወይም በጥሬ ገንዘብ እንዲያስይዙ ይደረጋል፡፡
- በመጀመሪያ ግልጽ ጨረታ በውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ ምክንያት የተያዘው ሀብት ከግልጽ ጨረታ የመነሻ ዋጋ በታች ሊሸጥ አይችልም፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው ወይም የጋራ ባለሀብቶች በጨረታው ለመሳተፍ አስፈላጊውን መስፈርት ካሟሉ እና በግልጽ ጨረታው ላይ ያቀረቡት ዋጋ ከከፍተኛ የግልጽ ጨረታው ዋጋ ጋር እኩል የሆነ እንደሆነ በአንደኛ ደረጃ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳው በሁለተኛ ደረጃ የጋራ ባለሀብቶች በቅድሚያ የመግዛት መብት ይኖራቸዋል፡፡
- አስተዳደሩ የተያዙ ሀብቶች የሚሸጡበት ዝርዝር አካሄድ የሚወስንና የጨረታ ስርአቱን የሚመራ የጨረታ ኮሚቴ ሊያቋቁም ይችላል፡፡
- የግልጽ ጨረታ አካሔድ ሥነ-ሥርዓት
በአስተዳደሩ የተያዘው ሀብት በግልጽ ጨረታ ሲሸጥ ጨረታው በሚከተለው አኳኋን ይከናወናል፡፡
- የግልጽ ጨረታው ማስታወቂያ በዚህ መመሪያ አንቀጽ 17(1) መሰረት እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
- የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነገረበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪዎች የጨረታ ሰነድ ማቅረብ አለባቸው፡፡
- የግልጽ ጨረታ ሰነድ ለማቅረቢያ በተወሰነው የመጨረሻ ቀን ሀብቱ የተያዘበት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋይ መሥሪያ ቤት ሀላፊ ወይም ወኪሉ በተገኘበት ግልጽ ጨረታው ይከፈታል ፡፡ ለመገኘት ፈቃደኛ ካልሆኑ በሌሉበት ጨረታው ይከናወናል፡፡
- ለግልጽ ጨረታው ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ዋጋ የሰጠው የጨረታው አሸናፊ ይሆናል፡፡
- የግልጽ ጨረታው ውጤት የፀና የሚሆነው የአስተዳደሩ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም የወከለው ሰው የጨረታውን ሪፖርት ሲያፀድቀው ይሆናል፡፡
- በድጋሚ (ሁለተኛ) ግልጽ ጨረታ ስለማውጣት
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ የተያዘው ሀብት በመጀመሪያ ግልጽ ጨረታ ያልተሸጠ እንደሆነ የአንደኛ ግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ በወጣው አኳኋን ሁለተኛ የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት እንዲሸጥ ይደረጋል፡፡
- ለድጋሚ የግልጽ ጨረታ ማስታወቂያ አፈፃፀም አግባብ ያላቸው የመጀመሪያ የግልጽ ጨረታ ሥርዓቶች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
- በሁለተኛ ግልጽ ጨረታ ስላልተሸጠ ሀብት
- ሀብቱ በሁለተኛ ግልጽ ጨረታ ያልተሸጠ እንደሆነ አስተዳደሩ በሚያቋቁመው የጨረታ ኮሚቴ የመንግስትን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ካመነበት አስተዳደሩ በግምቱ እንዲረከበው ወይም ሦስተኛና ከሦስተኛ በላይ ግልጽ ጨረታ እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡
- የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይም የወከለው ሰው ጨረታው በተለየ ሁኔታ በውስን ጨረታ እንዲፈፀም ካልወሰነ በስተቀር በሁለተኛው ግልጽ ጨረታ ያልተሸጠው ሀብት በሦስተኛ ወይም ከሦስተኛ ጊዜ በላይ በሚካሄድበት ጊዜ የግልጽ ጨረታውን መነሻ ዋጋ በመቀነስ ሀብቱ እንዲሸጥ ሊያደርግ ይችላል፡፡
- ሦስተኛ ወይም ከሦስተኛ ጊዜ በላይ የሚደረግ ግልጽ ጨረታ ሲካሄድ አግባብ ያላቸው የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ጊዜ የግልጽ ጨረታ ሥነ-ሥርዓቶች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
- የግልጽ ጨረታ አፈጻጸም ሪፖርት ስለማቅረብ
የጨረታ ኮሚቴ፡-
- ከዚህ መመሪያ ጋር አባሪ በሆነው ቅጽ በተመለከተው መሰረት የግልጽ ጨረታውን አካሄድ የሚያሳይ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
- ሪፖርቱን የግልጽ ጨረታው አስፈፃሚ ከሆነው ኃላፊ አስተያየት ጋር ለአስተዳደሩ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም ለወከለው ሰው ለውሳኔ ያቀርባል፡፡
- ሀብት በግልጽ ጨረታ ከተሸጠ በኋላ ስለሚፈፀም ተግባር
- የተያዘ ሀብት በግልጽ ጨረታ ከተሸጠና የጨረታው አሸናፊ ለጨረታ ማስከበሪያ ያስያዘውን ገንዘብ እና የውል ማስከበሪውን 10% እንዲሁም አጠቃላይ ያሸነፈበትን ዋጋ በዕለቱ ለአስተዳደሩ ባንክ ሂሳብ ገቢ ያደርጋል፡፡ ሌሎች ተሳታፊዎች ያስያዙት ገንዘብ ተመላሽ ይሆናል፡፡
- የግልጽ ጨረታ አሸናፊ ያሸነፈበትን የገንዘብ መጠን ለአስተዳደሩ በዕለቱ ገቢ ለማድረግ በበቂ ምክንያት ያልተቻለ እንደሆነ በዕለቱ ያልከፈለውን ቀሪ ክፍያ ግልጽ ጨረታው ከተካሄደበት ዕለት ጀምሮ በሚቆጠሩ 15 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ለአስተዳደሩ ገቢ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
- አሸናፊው ተጫራች በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 በተገለፀው ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን ለአስተዳደሩ ገቢ ካላደረገ የ7 ቀን ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልተከፈለ በጨረታ ወቅት ያስያዘው የውል ማስከበሪያ ገንዘብ ለአስተዳደሩ ገቢ የሚደረግ መሆኑ በፅሑፍ ይገልጽለታል፡፡
- የግልጽ ጨረታው አሸናፊ ማስጠንቀቂያው ከደረሰው ቀን ጀምሮ በ7 ቀን ጊዜ ውስጥ በልዩነት የሚፈለግበትን ሂሳብ ገቢ ካላደረገ ፤ በሁለተኛነት አሸናፊ የሆነው ተጫራች ያቀረበው ዋጋ ከመነሻ ዋጋው በታች ካልሆነ አሸናፊ ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው አሸናፊ ተጫራች ያስያዘው የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘብ ለአስተዳደሩ ገቢ ይደረጋል፡፡
- የግልጽ ጨረታው አሸናፊ ቀሪውን ሂሣብ ባለመክፈሉ ጨረታው የተሠረዘ እንደሆነ ጨረታው የመጀመሪያ ከሆነ የመጀመሪያ ግልጽ ጨረታ እንዳልተደረገ፣ ሁለተኛ ግልጽ ጨረታ ከሆነም ሁለተኛው ጨረታ ይሰረዛል፡፡
- የተሸጠውን ሀብት ለገዥው ስለማስረከብ
- አስተዳደሩ በግልጽ ጨረታ የተሸጠው ሀብት ዋጋ ሙሉ በሙሉ መከፈሉን ካረጋገጠ ተንቀሳቀሽ ሀብት ከሆነ ለአሸናፊው ወዲያውኑ ያስረክባል፡፡
- የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ የሸጠው ሀብት የማይንቀሳቀስ ወይም ልዩ ተንቀሳቃሽ ሀብትና የባለቤትነት ስም ለማዘዋወር ምዝገባ የሚያስፈልገው ከሆነ አስተዳደሩ የሀብት ባለቤትነት መብት በገዥው ስም እንዲዘዋወር አግባብ ላለው የመንግሥት አካል በጽሑፍ ያስታውቃል፡፡
- አስተዳደሩ በግልጽ ጨረታ የሸጠውን ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለእዳ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ሀብት መዝጋቢ አካላት ንብረቶች በገዥው ስም እንዲዛወር የሚሰጠውን ትዕዛዝ ባይፈጽሙ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች አግባብ ባለው ህግ መሰረት በህግ ይጠየቃሉ፡፡
- በግልጽ ጨረታ ያልተሸጠን ሀብት ስለማስረከብ
- በዚህ መመሪያ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 1) እንደተመለከተው ሊሸጥ ያልቻለ ሀብት አስተዳደሩ እንዲረከበው ውሳኔ የተሰጠ እንደሆነ፣ ይህንኑ ውሳኔ የሀብቱ ባለቤት በፅሑፍ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡
- አስተዳደሩ በግምቱ የተረከበውን ሀብት እስከሚሸጠው ድረስ ለአስተዳደሩ የተሻለ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ሊያከራይ ይችላል፡፡
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳን ስለማቀናነስ
- በግልጽ ጨረታ የተሸጠ ሀብት ወይም አስተዳደሩ የተረከበው ሀብት በተሸጠበት ወይም አስተዳደሩ በተረከበበት ዋጋ ልክ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ከሚፈለግበት ዕዳ እንዲቀነስ ይደረጋል፡፡
- በግልጽ ጨረታ ከተሸጠው ሀብት የተገኘ ገንዘብ በንዑስ አንቀጽ 1 በተመለከተው መሰረት እንዲቀናነስ ከተደረገ በኋላ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ ላይ የሚፈለግ ቀሪ ዕዳ ካለ፣ አስተዳደሩ ለዕዳው ክፍያ የሚውል ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩን ሌላ ማናቸውም ሀብት በመያዝ መሸጥ ይችላል፡፡
- በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀጽ 1 በተመለከተው መሰረት ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ የሚፈለግበት ውዝፍ የጡረታ መዋጮና ሌሎች ወጪዎች ከተቀነሱ በኋላ ተራፊ ገንዘብ ካለው ወዲያውኑ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ከፋዩ መስሪያ ቤት ይመልስለታል፡፡
- ሀብትን የመያዣና የመሸጫ ወጪዎች
- ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ባለዕዳውን ሀብት በመያዝ በመሸጥ ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ ክፍያ የማዋል ሥርዓት ወጪዎች የሚባሉት የሚከለተሉት ናቸው፡፡
ሀ) የተሸከርካሪ መጎተቻ ወጪ
ለ) የተያዙ ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የወጣ ወጪ
ሐ) የመጋዘን ወጪ ወይም ከሌሎች ውዝፍ የጡረታ መዋጮ ዕዳ ሀብት ጋር ከሆነ ወጪው ተሰልቶ
መ) የቁልፍ መቁረጫና አዲስ ቁልፍ መግዣ
ረ) ለአጫራቾች የአገልግሎት ወይም የስራ ማስኬጃ ክፍያ
ሰ) ዋጋ ማስገመቻ
ሸ) የጥበቃ ወጪ
ቀ) ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ልዩ ልዩ ወጪዎች ሲሆኑ ወጭውም በባለእዳው ይሸፈናል፡፡
ክፍል አራት
ልዩ ልዩ ድንጋጌ
- መሸጋገሪያ ድንጋጌ
ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት በአስተዳደሩ የተያዙ ወይም የተከበሩ ሀብቶች በዚህ መመሪያ መሰረት ፍጻሜ ያገኛሉ፡፡
- ሥነ ስርዓት ስለመዘርጋት
አስተዳደሩ ይህን መመሪያ ለማስፈጸም የሚረዳ የአሰራር ሥርዓት እንደ አስፈላጊነቱ ሊዘረጋ ይችላል፡፡
- የመመሪያው ተፈጻሚነት
ይህ መመሪያ -------------2016 ዓ/ም ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡